ቀጥታ፡

አሸባሪው ህወሓት መስጂዶችን የጦር ማዘዣና ምሽግ አድርጎ ተጠቅሟል

ታህሳስ 28 ቀን 2014 (ኢዜአ) አሸባሪው የህወሓት ቡድን ወረራ በፈጸመባቸው የአፋርና አማራ ክልሎች የሚገኙ መስጂዶችን የጦር ማዘዣና ምሽግ አድርጎ መጠቀሙን በኢትዮጵያ እስልምና ጉዳይ ጠቅላይ ምክር ቤት የተቋቋመ አብይ ኮሚቴ አስታወቀ፡፡

የአብይ ኮሚቴው አባልና የሚዲያና ኮሙዩኒኬሽን ንዑስ ኮሚቴ ሰብሳቢ አቶ መሃመድ ካሳ እንደገለጹት፤ አሸባሪ ቡድኑ በወረራ በቆየባቸው አካባቢዎች መስጂዶችን የጦር ማዘዣና ምሽግ አድርጎ ተጠቅሟል።

በመስጂዶች ላይ እጅግ አስነዋሪ ድረጊት መፈጸሙንም ጠቁመዋል፡፡

ኢትዮጵያ በዓለም አቀፍ ደረጃ የሚታወቁ ቅርሶች ባለቤት መሆኗን የጠቀሱት አቶ መሃመድ፤ በኢትዮጵያ የሚገኙት ቅርሶች፣ አስተሳሰቦችና እምነቶችን መንካት የዓለም ታሪክና ቅርስን መንካት መሆኑን አስረድተዋል፡፡

ዓለም አቀፍ ሚዲያዎች የኢትዮጵያ ቤተ- እምነቶች ሲወድሙ ዝምታን  መምረጣቸው ተገቢ አይደለም  ሲሉ ወቅሰዋል፡፡

የሰው ልጅ ለፈጣሪው ጸሎትና ምስጋና የሚያቀርብበትን የእምነት ተቋማትን የጦር ምሽግ ማድረግ ፍጹም ተቀባይነት የሌለው ህገወጥ ድርጊት መሆኑንም ጨምረው ገልጸዋል።

በቀጣይም የደረሰውን ጉዳት በዝርዝር በማጥናት ህጉ በሚፈቅደው መሰረት እስከ ዓለም አቀፍ ተቋማት ድረስ የጉዳቱን መጠን የማሳወቅ ስራ እንደሚሰራ አስታውቀው፤ ተገቢውን ጥናት በማድረግ የተጎዱ ቤተ እምነቶችንና ሃብቶችን መልሶ የመገንባት ስራ እንደሚከናወን ተናግረዋል።

ኢትዮጵያን እናልማ፣ እንገንባ፣ እንዘጋጅ‼

ሀገርን በዘላቂነት እናልማ‼

የፈረሰውን አብልጠን እንገንባ‼

ለማንኛውም ፈተና እንዘጋጅ‼

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም