በደቡብ አፍሪካ የሚኖሩ ኢትዮጵያውያንና ትውልደ ኢትዮጵያውያን ወደ ኢትዮጵያ እየገቡ ነው - ኢዜአ አማርኛ
በደቡብ አፍሪካ የሚኖሩ ኢትዮጵያውያንና ትውልደ ኢትዮጵያውያን ወደ ኢትዮጵያ እየገቡ ነው
ታህሳስ 28 ቀን 2014 (ኢዜአ) በደቡብ አፍሪካ የሚኖሩ ኢትዮጵያውያንና ትውልደ ኢትዮጵያውያን ጠቅላይ ሚኒስትር አቢይ አህመድ ያቀረቡትን ‘የአንድ ሚሊዮን የዳያስፖራ የአገር ቤት ጉዞ” ጥሪ ተቀብለው ወደ ኢትዮጵያ መግባታቸውን ቀጥለዋል።
100 አባላትን ያቀፈ የደቡብ አፍሪካ የዳያስፖራ ልዑክ ትናንት ማምሻውን ኢትዮጵያ ሲገባ በአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር የዳያስፖራ ማዕከል አቀባበል ተደርጎለታል።
ልዑካን ቡድኑ በጉዟቸው ወቅት ያሰባሰቡትን ከሶስት ሺህ በላይ የአሜሪካን ዶላር እና 23 ሺህ የደቡብ አፍሪካ ራንድ ለአገር መከላከያ ሰራዊት ገቢ እንዲሆን በቦሌ ዓለም አቀፍ አየር ማረፊያ በሚገኘው የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ አገልግሎት መስጫ ክፍል በኩል ገቢ ማድረጋቸውን ኢዜአ ከተባባሩት የኢትዮጵያ ማህበረሰብ ማህበር በደቡብ አፍሪካ (ዩካሳ) ያገኘው መረጃ ያመለክታል።
ከመጡት ውስጥ በግለሰብ ደረጃ የመድሐኒትና አልባሳትን ድጋፍ እንዳደረጉም አመልክቷል።
የተባባሩት የኢትዮጵያ ማህበረሰብ ማህበር በደቡብ አፍሪካ ሃላፊ ፕሮፌሰር ሙላቱ ፈቃዱ ዳያስፖራው መንግስት ባዘጋጃቸው የዳያስፖራ መርሃ ግብሮች ላይ የነቃ ተሳትፎ ያደርጋሉ ብለዋል።
በደቡብ አፍሪካ የሚገኙ የኢትዮጵያ ዳያስፖራ ማህበረሰብ አባላት ኢትዮጵያ አሁን ካለችበት ተጨባጭ ሁኔታ አኳያ በፐብሊክ ዲፕሎማሲው መስክ፣ ወደ አገር ቤት ግቡ ጥሪን በመቀበል እንዲሁም ሀብት በማሰባሰብ ተግባራዊና ወቅታዊ ምላሾችን በመስጠት ላይ እንደሚገኝ ማህበሩ አስታውቋል።
ኢትዮጵያ ያደረገችውን ጥሪ ተከትሎ የትናንቱን ጨምሮ በደቡብ አፍሪካ የሚኖሩ 250 የኢትዮጵያ ዳያስፖራ ማህበረሰብ አባላት ወደ አገር መግባታቸውንም ጠቁሟል።
በደቡብ አፍሪካ ያለውን የአገር ቤት ጉዞ ጥሪ በደቡብ አፍሪካ የኢትዮጵያ ኤምባሲ፣ የተባባሩት የኢትዮጵያ ማህበረሰብ ማህበር በደቡብ አፍሪካ (ዩካሳ)፣ የእምነት ተቋማትና የሚዲያ አካላት በማስተባበር ላይ እንደሚገኙ ተገልጿል።
ኢትዮጵያን እናልማ፣ እንገንባ፣ እንዘጋጅ‼
ሀገርን በዘላቂነት እናልማ‼
የፈረሰውን አብልጠን እንገንባ‼
ለማንኛውም ፈተና እንዘጋጅ‼