ለሶስት መቶ ቤተሰቦች የአፋር ባህላዊ ቤቶችን እየገነቡ የሚገኙት በጎ አድራጊዋ እንስት - ኢዜአ አማርኛ
ለሶስት መቶ ቤተሰቦች የአፋር ባህላዊ ቤቶችን እየገነቡ የሚገኙት በጎ አድራጊዋ እንስት
አዲስ አበባ፣ ታህሳስ 28/2014 ( ኢዜአ) በችግር ውስጥ ያሉ ሴቶችን ከመርዳት የማያርፉት ወይዘሮ አስቴር ዘውዴ ለ300 ቤተሰቦች የአፋር ባህላዊ ቤቶችን (ዳቦይታ) በመገንባት ለወገን ደራሽነታቸውን በተግባር እያሳዩ ነው፡፡
ወይዘሮ አስቴር ዘውዴ ለሰላሳ ዓመታት በተባበሩት መንግስታት ድርጅት የሴቶች ጉዳይን በሚመለከቱ የስራ መስኮች ላይ አገልግለዋል፡፡
በዚህ ስራቸው ከበለጸጉ እስከ ደሃ አገራት ድረስ የሴቶችን ሁኔታና በሴቶች ላይ የሚደርሰውን በደል ተመልክተዋል፤ለመብቶቻቸውም ታግለዋል።
ከስራቸው በጡረታ ከተገለሉ በኃላም ወደ ኢትዮጵያ ተመልሰው ላለፉት አስራ አንድ ዓመታት በተለያዩ ምክንያቶች ጉዳት የደረሰባቸውን ሴቶች እየረዱ ይገኛሉ፡፡
''ፀሀይ ዘውዴ ሜሞሪያል ስኮላርሺፕ'' በተሰኝ የድጋፍ መርሃ-ግብር ማዬት የተሳናቸው ሴት ተማሪዎችን በገንዘብና በትምህርት ቁሳቁስ ሲደግፉ መቆየታቸውን ነው ለኢዜአ የተናገሩት፡፡
ወይዘሮ አስቴር ዘውዴ እንደሚሉት፤ በጦርነትና ግጭት ወቅት ሴቶችና ህጻናት ከየትኛውም የህብረተሰብ ክፍል ይበልጥ ተጎጂዎች ናቸው፡፡
በአፋር ክልል በአሸባሪው የሕወሓት ወራሪ ኃይሎች ጉዳት የደረሰባቸውን አካባቢዎች መጎብኘታቸውን የሚናገሩት ወይዘሮ አስቴር፤ በጉብኝታቸውም በርካታ ዜጎች እጅግ ልብ በሚነካ ችግር ውስጥ ሆነው መመልከታቸውን አንስተዋል።
''በክልሉ ጭፍራ ወረዳ ከ4 ቀበሌዎች ተፈናቅለው ማዴራ በሚባል ሜዳ ላይ በችግር ውስጥ ህይወታቸውን እየገፉ የሚገኙ 1 ሺህ 680 ቤተሰቦችን ተመለከትኩ'' ይላሉ።
በመሆኑም እነዚህ ወገኖች አስቸኳይ እገዛ እንደሚፈልጉ ተገንዝበው አቅማቸው በፈቀደ መጠን ለመርዳት እንቅስቃሴ መጀመራቸውን ይናገራሉ።
በዚህም አገር ውስጥም ውጭም የሚኖሩ ከ50 በላይ የሚሆኑ ወዳጆቻቸውን አስተባብረው ሁለት ሳምንት ባልሞላ ጊዜ ውስጥ አንድ ሚሊዮን ብር ቃል እንደተገባላቸው ገልጸው፤ ከዚህ ውስጥ 870 ሺህ ብር በአጭር ጊዜ ውስጥ ገቢ መደረጉን አንስተዋል።
በተገኘው ገንዘብም ለአንድ ተፈናቃይ ቤተሰብ የአፋር ባህላዊ ጎጆ በአካባቢ አጠራር 'ዳቦይታ' ለመስራት የሚያበቃ ሰሌን በ3 ሺህ ብር ገዝቶ ማቅረብ መሆኑን ተናግረዋል።
የአፋር ሴቶች ተፈጥሮ የለገሰቻቸውን ድንቅ ጥበብ ተጠቅመው ለቤተሰባቸው የሚበቃ ጎጆ የሚቀልሱ ሲሆን፤ ከዚህ አኳያ ድጋፍ ሴቶችን ማገዝ ነው ይላሉ ወይዘሮ አስቴር።
ሁኔታው ተፈናቃይ ወገኖቻችን በቀን ከፀሀይ ሀሩርና በማታ ከንፋስና ከአውሬ ከለላ እንዲያገኙ ማድረግ የሚያስችል ነው ብለዋል።
በዚህ ስራቸው እስከ ባለፈው ሳምንት ድረስ 54 ባህላዊ ቤቶችን መገንባት የቻሉ ሲሆን በሚቀጥሉት ሶስት ሳምንታት ጊዜ ውስጥ በአጠቃላይ ለ300 ቤተሰቦች ቤቶቹን ገንብቶ ለማጠናቀቅ እየተንቀሳቀሱ ይገኛሉ።
አሸባሪ ቡድኑ ካደረሰው ጉዳት አንጻር በርካታ ሴቶችና ህጻናትን መታደግ እንደሚያስፈልግ አንስተው፤ በዚህም አቅም ያላቸው ኢትዮጵያውያን የሚችሉትን ሁሉ እንዲያደርጉ ጥሪ አቅርበዋል።
ወይዘሮ አስቴር የሚያደርጉትን ጥረት የአፋር አርብቶ አደሮች ልማት ማሕበር በአጋርነት እየሰራ መሆኑንም ጠቅሰዋል።