የሰዎች ለሰዎች ድርጅት እና መቄዶንያ የበጎ አድራጎት ማህበር ከ45 ሚሊዮን ብር በላይ የሚገመት ድጋፍ አደረጉ

ባህር ዳር ፣ታህሳስ 28/2014(ኢዜአ) የሰዎች ለሰዎች ግብረ ሰናይ ድርጅት እና መቄዶንያ የበጎ አድራጎት ማህበር በአማራ ክልል ለወደሙ ሆስፒታሎችና ለተፈናቀሉ ወገኖች የሚውል ከ45 ሚሊዮን ብር በላይ የሚገመት የዓይነት ድጋፍ አደረጉ።

ከድጋፉ ውስጥ የሰዎች ለሰዎች ግብረ ሰናይ ድርጅት  ከ25 ሚሊዮን ብር በላይ ወጭ የተደረገባቸው መድሃኒቶችና የሕክምና ቁሶች ሲሆን ቀሪው መቄዶንያ የበጎ አድራጎት ማህበር ነው።

የአማራ ክልል ርዕሰ መስተዳድር ዶክተር ይልቃል ከፍአለ በድጋፍ ርክክብ ሥነ-ሥርዓቱ ላይ እንዳሉት የአሸባሪው ህወሓት ቡድን በክልሉ ሰብአዊና ቁሳዊ ውድመት ፈጽሟል።

በአሁኑ ወቅት በመከላከያና ሌሎች የጸጥታ ሀይሎች በተወሰደበት እርምጃ የሽብር ቡድኑ ተሸንፎ ከአብዛኛው የክልሉ አካባቢዎች ለቆ ቢወጣም የመልሶ ማቋቋም እና መልሶ ግንባታው ሥራው የኢትዮጵያን ህዝብና አጋር አካላትን ርብርብ እንደሚጠይቅ ተናግረዋል።

የሰዎች ለሰዎች ድርጅት ያደረገው የሕክምና ቁሳቁስና የመድሃኒት ድጋፍ ጉዳት የደረሰባቸውን ሆስፒታሎች ስራ በማስጀመር ለህብረተሰቡ መሰረታዊ ጤና አገልግሎት ለመስጠት እንደሚያግዝ ገልጸዋል።

"መቄዶንያ የበጎ አድራጎት ማህበር ለአረጋዊያንና ለአዕምሮ ህሙማን ከሚያደርገው ሁለንተናዊ እንክብካቤ ባለፈ የተፈናቀሉ ወገኖችን ለመደገፍ ያሳየው ተነሳሽነት ክብር የሚገባው ነው" ብለዋል።

"መላው የኢትዮጵያ ህዝብ ከጎናችን በመሆኑ የወደመውን ገንብተን በአዲስ መንፈስ ወደ ስራ የምንገባበት እንጂ የምንቆዘምበት አይደለም" ሲሉም ለክልሉ ህዝብ መልዕክት አስተላልፈዋል።

የሰዎች ለሰዎች ግብረ ሰናይ ድርጅት የሀገር አቀፍ ተጠሪ አቶ ይልማ ታዬ በበኩላቸው፤ ድርጅታቸው ከ25 ሚሊዮን ብር በላይ ወጭ የተደረገባቸው መድሃኒቶችና የሕክምና ቁሶችን ድጋፍ ማመቻቸቱን  ተናግረዋል።

የተደረገው ድጋፍ ከሰሜን ሸዋ ዓለም ከተማ እስከ ሰሜን ወሎ ወልድያ የወደሙ ስምንት ሆስፒታሎችን ሥራ ለማስጀመር የሚያስችል መሆኑን አመልክተዋል።

ድርጅቱ በአማራ እና አፋር ክልሎች ለተፈናቀሉ ወገኖችና ለተጎዱ ተቋማት የሚውል የዛሬውን ጨምሮ እስካሁን ድረስ ከ85 ሚሊዮን ብር በላይ የዓይነት ድጋፍ አድርጓል።

ምንም እንኳ ድርጅቱ በዘላቂ ልማት ላይ አተኩሮ የሚሰራ ቢሆንም በአሁኑ ወቅት ከተፈጸመው ውድመትና ዘረፋ አንጻር በዕለት ድጋፍና በመልሶ ግንባታ ሥራው እየተሳተፈ መሆኑን ተናግረዋል።

"በአማራ እና አፋር ክልሎች የደረሰውን ጉዳት ለመመለስ አመራሩና ህብረተሰቡ 24 ሰዓት መስራት አለባቸው" ያለው ደግሞ የሰዎች ለሰዎች ግብረ ሰናይ ድርጅት የበጎ ፈቃድ አምባሳደር ሻለቃ ሃይሌ ገብረ ስላሴ ነው።

ወቅቱ መላው የኢትዮጵያ ህዝብ በመልሶ ግንባታውና በማቋቋም ሥራው ለመሳተፍ የተነቃነቀበት ጊዜ መሆኑን ጠቁሞ፤ "ይህን መልካም አጋጣሚ ለዘላቂ ልማትና እድገት መጠቀም ይገባል" ብሏል።

ከዋግ ኽምራ ዞን ለተፈናቀሉ ወገኖች የሚውል ከ20 ሚሊዮን ብር በላይ የሚገመት የምግብ፣ የአልባሳትና ሌሎች ድጋፎችን ይዘው መምጣታቸውን የገለጹት ደግሞ የመቄዶንያ በጎ አድራጎት ማህበር የክልል ጉዳዮች ዋና ዳይሬክተር አቶ ማህተመ በቃሉ ናቸው።

ማህበሩ ጧሪ ቀባሪ ያጡ አረጋውያንንና የአዕምሮ ህመምተኞችን በመንከባከብ ላይ የተሰማራ መሆኑንም አውስተዋል።

በክልሉ አሸባሪው ህወሓት በወረራ በቆየባቸው የተለያዩ አካባቢዎች ያደረሳቸው ሰብአዊና ቁሳዊ ጉዳቶች ለማወቅ የጥናት ሥራ መጀመሩን ኢዜአ ቀደም ብሎ ዘግቧል።  

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም