በውጭ ሀገር ሰርተን ያገኘነውን ሃብት በማካፈል አጋርነታችንን እንቀጥላለን - ኢዜአ አማርኛ
በውጭ ሀገር ሰርተን ያገኘነውን ሃብት በማካፈል አጋርነታችንን እንቀጥላለን
ታኅሳስ 27 ቀን 2014 (ኢዜአ) በውጭ ሀገር ሰርተን ያገኘነውን ሃብት ለወገኖቻችን በማካፈል አጋርነታችንን እንቀጥላለን ሲሉ ከአሜሪካ ወደ ሀገር ቤት የገቡ ዳያስፖራዎች ገለጹ።
ከአሜሪካ ዋሺንግተን ዲሲ ወደ አዲስ አበባ የገቡት ዳያስፖራዎቹ በአውሮፕላን ውስጥ በጉዞ ላይ እንዳሉ ከ11 ሺህ በላይ ዶላር አሰባስበዋል።
በጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ አህመድ ጥሪ መሰረት በርካታ ዳያስፖራዎች ወደ ሀገር ቤት እየገቡ ይገኛሉ፡፡
ዳያስፖራዎቹ ለሀገራቸው ያላቸውን አለኝታነት የህክምና መድሃኒትን ጨምሮ ልዩ ልዩ ድጋፎችን በማድረግ እያሳዩ ይገኛሉ።
ከአሜሪካን ዋሽንግተን ዲሲ ወደ አዲስ አበባ እየተጓዙ የነበሩ ኢትዮጰያውያንና ትውልደ ኢትዮጵያውያን ያሰባሰቡትን ከ11 ሺህ ዶላር በላይ በቦሌ አለም አቀፍ አውሮፕላን ማረፊያ በሚገኘው የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ አይዞን ኢትዮጵያ አካውንት ገቢ አድርገዋል።
ከእንግዶቹ አንዷ የሆኑት ወይዘሮ ኢየሩሳሌም ኃይሉ በዚሁ ወቅት በምንኖርበት ሀገር ሰርተን ያፈራነውን ሃብት ለሀገራችንና ለወገኖቻችን እናካፍላለን ብለዋል።
ያደረጉት ድጋፍ የመጀመሪያቸው እንደሆነ በመግለጽ፣ በቀጣይም እገዛቸውን በተጠናከረ መልኩ በማስቀጠል አለኝታነታቸውን እንደሚያሳዩ ገልጸዋል።
ድጋፉን ካደረጉት መካከል ወይዘሮ መዓዛ አበጋዝ በበኩላቸው በቅርብ ጊዜ ኢትዮጵያ እንደነበሩ ገልጸው፤ የጠቅላይ ሚኒስትሩን ጥሪ ተቀብለው በ1 ወር ጊዜ ውስጥ ተመልሰው መምጣታቸውን አንስተዋል።
ኢትዮጵያውያን ሀገራቸው ስትነካ እንደማይወዱ ተናግረው፤ የአሁኑ ትውልድ ለሀገሩ በመረባረብ የሚያሳየው አለኝታነት እንደሚያኮራ ገልጸዋል።