ቀጥታ፡

ኢትዮጵያ የምትሻውን ሙያዊም ሆነ ሰብአዊ እገዛ ሁሉ ለማድረግ ተዘጋጅተናል

ታህሳስ 27 ቀን 2014 (ኢዜአ) ኢትዮጵያ የምትሻውን ሙያዊም ሆነ ሰብአዊ እገዛና ድጋፍ ለማድረግ ዳያስፖራው መዘጋጀቱን በአሜሪካ ዳላስ-ቴክሳስ የኢትዮጵያ ግብረ-ሃይል አስተባባሪ ተናገሩ።

ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አህመድ ያደረጉትን ጥሪ ተከትሎ በተለያዩ የዓለም ሀገራት የሚኖሩ ኢትዮጵያውያን፣ ትውልደ ኢትዮጵያውያንና የኢትዮጵያ ወዳጆች ወደ ሀገር ቤት በመግባት ላይ ይገኛሉ።

በመሆኑም ኢትዮጵያ የምትሻውን ሙያዊም ሆነ ሰብአዊ እገዛና ድጋፍ ለማድረግ ዳያስፖራው ተዘጋጅቶ ወደ ሀገር ቤት መግባቱን በአሜሪካ ዳላስ-ቴክሳስ የኢትዮጵያ ግብረ-ሃይል አስተባባሪ መላኩ ዳምጤ ተናግረዋል።

በአሜሪካ የሚኖሩ ዳያስፖራዎችም የህክምና እርዳታ መስጫና ሌሎችም አስፈላጊ ቁሳቁሶችን ከጤና ሚኒስቴር ጋር በመተባበር ድጋፍ ሲያደርጉ መቆየታቸውን አስታውሰዋል።

አሁን ወደ ሀገር ቤት ሲገቡም ተመሳሳይ ድጋፎችንና ሌሎች አገልግሎቶችን ለመስጠት ተዘጋጅተዋል ነው ያሉት።

ኢትዮጵያ በአሁኑ ወቅት የልጆቿን እርዳታ ከምንጊዜውም በላይ የምትሻበት ወቅት ላይ እንደመሆኗ ዳያስፖራው የሚጠበቅበትን ድጋፍ ለሀገሩ ለመስጠት ከፍተኛ ተነሳሽነት እንዳለው ገልጸዋል።

የችግሩ ዋነኛ ሰለባ በሆኑት በአፋር እና በአማራ ክልሎች ላይ ለሚገኙ ዜጎች የሚውሉ ግብአቶችንም ቦታው ድረስ በመሄድ ለማህበረሰቡ እንደሚደርሱ ጠቅሰዋል።

የተለያዩ የቱሪስት መስህብ የሆኑ ቦታዎችና መዳረሻዎችን በመጎብኘትም ቱሪዝሙን ለማነቃቃት ድርሻ ይኖራቸዋል ነው ያሉት።

በቅርቡ በዳላስ በተደረገ የገቢ ማሰባሰቢያ መርሃ ግብር ከ450 ሺህ ዶላይ በላይ መገኘቱን አስታውሰው ድጋፉ ተጠናክሮ እንደሚቀጥል አረጋግጠዋል።

በኢትዮጵያ ዳያስፖራው በረጅም ቆይታ ያካበተውን እውቀትና ሀብት የሚያለማበት መንግስት ምቹ ሁኔታ መፍጠሩ ይታወቃል።

ኢትዮጵያን እናልማ፣እንገንባ፣እንዘጋጅ

‼️

ሀገርን በዘላቂነት እናልማ

‼️

የፈረሰውን አብልጠን እንገንባ

‼️

ለማንኛውም ፈተና እንዘጋጅ

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም