ቀጥታ፡

''ልጆቿ ሀገር ለማዳን ስንሰባሰብ ኢትዮጵያ በሀሴት የምትመለከት እናት ሆና ትታየናለች'' የዲፌንድ ኢትዮጵያ-ግብረ ኃይል

ታህሳስ 27 ቀን 2014 (ኢዜአ) ልጆቿ በአንድነት ሀገር ለማዳን ስንሰባሰብ ኢትዮጵያ በሀሴት የምትመለከት እናት ሆና ትታየናለች ሲሉ ከዩናይትድ ኪንግደም ወደ ኢትዮጵያ የገቡ የዲፌንድ ኢትዮጵያ ግብረ ኃይል አባላት ገለጹ።

''ዲፌንድ ኢትዮጵያ ኢሮፕ'' የተሰኘው ግብረ-ኃይል በኢትዮጵያ ላይ እየበረታ የመጣውን የውጭ ጫና በመቃወም ሀገር በሚያስፈልጋት ሁሉ ተሳትፎ ሲያደርግ ቆይቷል።

የጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር ዐቢይ አህመድ ጥሪን ተከትሎ በርካታ ቁጥር ያላቸው የግብረሀይሉ አባላት አዲስ አበባ ገብተዋል።

ከዩናይትድ ኪንግደም የመጡት የዲፌንድ ኢትዮጵያ አባል ወይዘሮ ባንቺአምላክ ይልማ፣ ወደ ኢትዮጵያ ሲገቡ ባዩት ነገር ሁሉ መደነቃቸውን ገልጸዋል።

ችግር በመጣ ጊዜ በአንድነት መቆም የኢትዮጵያውያን መገለጫ መሆኑን በመግለጽ “ኢትዮጵያ ይህንን አንድነት የምትመለከት እናት ትመስለኛለች” ሲሉ ገልጸዋል።

በሀገር ቤት ቆይታቸውም አሸባሪው ህወሃት በሀገር ላይ የቃጣውን ጦርነት ለመመከት ለሀገር መሰዋዕት ለሆኑ የመከላከያና ሌሎች የጸጥታ አካላት ልጆች ድጋፍ እንደሚያደርጉ ገልጸዋል።

በዚህም በአማራና አፋር ክልሎች ወላጆቻቸውን ያጡ እድሜያቸው ከ8 እስከ 12 ዓመት የሆኑ 20 ህጻናትን እንደሚያስተምሩና ራሳቸውን እስኪችሉ ድረስ እንደሚያሳድጓቸው ተናግረዋል።

የዲፌንድ ኢትዮጵያ አስተባባሪ አቶ ዘላለም ተሰማ፣ ኢትዮጵያዊነት ማለት ጀግንነትና አልበገርም ባይነት እንደሆነ ለዓለም እያሳየን ነው ብለዋል።

ዲፌንድ ኢትዮጵያም በዩናይትድ ኪንግደም ደጀን ሆኖ ሰፊ ተሳትፎ ሲያደርግ እንደቆየ በማንሳት በቀጣይም ሀገር በምትፈልገው ሁሉ ለማገዝ በአካል መገኘታቸውን ገልጸዋል።

የዲፌንድ ኢትዮጵያ አባል ወይዘሮ ዓለም ረታ በበኩላቸው፣ ከስራ ገበታቸው ለተወሰነ ጊዜ በመራቅ ኢትዮጵያን ለማገልገል ወደ ሀገር እንደገቡ ገልጸዋል።

በቆይታቸውም ወደ አማራና አፋር ክልል በመንቀሳቀስ እገዛ እንደሚያደርጉ ገልጸዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም