ቀጥታ፡

አሸባሪው ህወሓት በእስልምና እምነት ተቋማት ላይ ያደረሰውን ውድመት የሚያጠና ቡድን ስራ ጀመረ

ታህሳስ 27 ቀን 2014 (ኢዜአ)አሸባሪው ህወሓት በእስልምና እምነት ተቋማት ላይ ያደረሰውን የቅርስና ቁሶች ውድመት የሚያጠና ቡድን ተቋቁሞ ስራ መጀመሩን የኢትዮጵያ እስልምና ጉዳዮች ጠቅላይ ምክር ቤት ገለጸ።

በኢትዮጵያ እስልምና ጉዳዮች ጠቅላይ ምክር ቤት የኡላማዎች ምክር ቤት ዋና ጸሃፊ ሸህ ቃሲም መሃመድ ጉዳዩን በማስመልከት መግለጫ ሰጥተዋል።

በመግለጫቸውም አሸባሪው ህወሃት በእምነቱ ተቋማት ቅርሶችና ንብረቶች ላይ ያደረሰውን ውድመት ለማጥናት የተቋቋመው ቡድን አንድ ዐቢይ ኮሚቴና አራት ንዑሳን ኮሚቴዎች እንዳሉት ገልጸዋል።

ከተቋቋሙት ኮሚቴዎች መካከል የጥናት ቡድን ንዑስ ኮሚቴ በነገው ዕለት ወደ አፋር ክልል በመጓዝ ስራውን እንደሚጀምር ተናግረዋል፡፡

ንዑስ ኮሚቴው በአፋርና አማራ ክልል በእስልምና እምነት የእውቀት ማዕከላት፣ በመስጊዶች፣ በታሪካዊ ቅርሶች ፣ቁሶች፣ በቁርአንና ሌሎች መጻሕፍት፣ መሻኢካዎች እና ሌሎችም ላይ የደረሰውን ጉዳትና ውድመት መጠንና ጥልቀት ያጠናል ብለዋል፡፡

የጉዳቱ መጠንና ሁኔታ ከተለየ በኋላ መልሶ የመገንባት ስራና ጉዳዩን የፈጸመው አካል በህግና በታሪክ ተጠያቂ እንዲሆን ተሰንዶ ይቀመጣል ነው ያሉት፡፡

ኮሚቴው ተቋቁሞ ወደ ስራ ከመግባቱ በፊት የዳሰሳ ጥናት በማድረግ ከፍተኛ ጉዳት ስለመድረሱ መረጋገጡን አስረድተዋል፡፡

የተቋቋመው ቡድን ከጠቅላይ ምክር ቤቱ ውጭ የሆኑ ባለሙያዎች የተካተቱበት መሆኑን ጠቅሰዋል።

የተቋቋመው የጥናት ቡድን በሚጓዝባቸው አካባቢዎች መንግስታዊና መንግስታዊ ያልሆኑ ድርጅቶች እንዲሁም ህብረተሰቡ ድጋፍ እንዲያደርግም ጠይቀዋል።

አሸባሪው ህወሃት በአማራና አፋር ክልሎች በወረራ በቆየባቸው አካባቢዎች በእስልምና ሃይማኖት ተቋማትና መስጊዶች ላይ ከፍተኛ ጉዳት በማድረስ ቅዱስ ቁርአንን ጭምር በማቃጠል የህዝብ ጠላት መሆኑን በተግባር ማሳየቱ ይታወቃል።

ኢትዮጵያን እናልማ፣እንገንባ፣እንዘጋጅ

‼️

ሀገርን በዘላቂነት እናልማ

‼️

የፈረሰውን አብልጠን እንገንባ

‼️

ለማንኛውም ፈተና እንዘጋጅ

‼️

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም