ቀጥታ፡

በወረራው የደረሰውን ሰብአዊና ቁሳዊ ውድመት በማስጠናት ይፋ ለማድረግ እየተሰራ ነው

ባህርዳር፣  ታህሳስ 27/2014 (ኢዜአ) አሸባሪው ህወሃት በወረራቸው አካባቢዎች ያደረሰውን ሰብአዊና ቁሳዊ ውድመትና ዝርፊያ በዩኒቨርሲቲዎችና በሌሎች ባለሞያዎች በማስጠናት ለህዝብና ለሚመለከታቸው አካላት ይፋ ለማድረግ እየተሰራ መሆኑን የአማራ ክልል የፕላንና ልማት ቢሮ አስታወቀ።

በጥናት ግኝት ላይ ተመስርቶ በሚካሄደው የመልሶ ማቋቋምና ግንባታ ተግባር መላው ኢትዮጵያዊያንና አጋር አካላት በገንዘብ፣ ቁሳቁስና በሌሎች ድጋፎች በንቃት እንዲሳተፉ ጥሪ ቀርቧል።

የአማራ ክልል የፕላንና ልማት ቢሮ ሃላፊ አቶ አንሙት በለጠ ለኢዜአ እንደገለጹት አሸባሪው ህወሃት ኢትዮጵያን ለማፍረስ የያዘውን ግብ ለማሳካት በአማራና አፋር ክልሎች ላይ ወረራ በመፈጸም መጠነ ሰፊ ጉዳት አድርሷል።

የጉዳቱን መጠንና ስፋት ለመለየት በክልሉ የሚገኙ አስር ዩንቨርሲቲዎች፣ ከፍተኛ ባለሙያዎችና የማዕከላዊ ስታቲስቲክስ ባለስልጣን ሰራተኞች የተሳተፉበት ጥናት እየተካሄደ መሆኑን ተናግረዋል።

በሰባት ዞኖችና በሁለት ከተማ አስተዳደሮች ቤት ለቤት ጭምር በሚካሄደው ጥናት የወረዳና የቀበሌ ባለሙያዎችና ድጋፍ ሰጭዎችን ሳይጨምር 1ሺህ 887 ባለሙያዎች መሳተፋቸውን አመልክተዋል።

ጥናቱን ማካሄድ ያስፈለገበት ዋና ዓላማ ጉዳቱን በትክክለኛ መረጃ ላይ ተመስርቶ በስትራቴጅክ እቅድ የታገዘ የመልሶ ግንባታ ስራ ለማከናወንና የተፈጸመውን ኢ-ሰብአዊ ድርጊት በታሪክ ሰንዶ ለማስቀመጥ መሆኑን ተናግረዋል።

በተጨማሪም አሻባሪው የህወሃት ቡድን በክልሉ ህዝብ ላይ ባደረሰው ሰብአዊ፣ ቁሳዊና ስነ ልቦናዊ ጉዳት ልክ በህግ እንዲጠየቅ ለማስቻል መሆኑን አመልክተዋል።

"የጊዜ ጉዳይ ነው እንጂ አሸባሪው ህወሃት መጠየቁ አይቀርም" ያሉት አቶ አንሙት ለዚህም የጥናቱን ግኝት በአግባቡ ማዘጋጀትና መሰነድ ተገቢ መሆኑን አስገንዝበዋል።

የቢሮው ሀላፊ አክለው አሸባሪው ህውሃት ኢትዮጵያን ለማፍረስ የያዘውን ግብ ለማሳካት ሲል በአማራና አፋር ክልሎች ወረራ ቢፈጽምም ጥቃቱ የመላው የኢትዮጵያ ህዝብ መሆኑን ተናግረዋል።

በጥናቱ ግኝት ላይ  ተመስርቶ  በሚካሄደው የመልሶ ማቋቋምና ግንባታ ስራ መላው የኢትዮጵያ ህዝብ  በንቃት እንዲሳተፍ የቢሮ ሃላፊው ጥሪ አቅርበዋል።

በውጭ የሚኖሩ ኢትዮጵያውያን፣ ትውልደ ኢትዮጵያውያንና ሌሎች ወዳጅ ሀገራት የደረሰውን ጉዳት ባጭር ጊዜ ውስጥ ገንብቶ ለህዝባዊ አገልግሎት ለማዋል የበኩላቸውን ድርሻ እንዲወጡም ነው የጠየቁት።

ከ40 በላይ ሆስፒታሎችን ጨምሮ ሌሎች የጤና ተቋማት፣ ከ4ሺህ በላይ ትምህርት ቤቶች ላይ ወራሪው ቡድን ዝርፊያና ውድመት መፈጸሙን ጠቅሰዋል።

ከመሰረታዊ የጤና አገልግሎት ውጭ የሆነውን ከ5 ሚሊየን በላይ ህዝብና ከትምህርት ውጭ የሆኑ ከ1 ነጥብ 9 ሚሊየን በላይ ተማሪዎችን ተጠቃሚ ለማድረግ በመልሶ ግንባታው መሳተፍ እንደሚያስፈልግ አንስተዋል።

እንደ ቢሮው ሀላፊ ገለጻ የተዘረፉና የወደሙ የህክምና መሳሪያዎች፣ የትምህርት ቁሳቁሶችና የቢሮ መገልገያዎችን ሁሉ ለማሟላት የመላ ህዝብንና በውጭ የሚኖሩ ኢትዮጵያዊያንና ትውልደ ኢትዮጵያዊያን  ንቁ ተሳትፎ ይጠይቃል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም