የኢትዮጵያ ታሪኮች የጋራ ማንነት መገለጫዎች እንጂ የልዩነት መንስኤ ሊሆኑ አይገባም - ኢዜአ አማርኛ
የኢትዮጵያ ታሪኮች የጋራ ማንነት መገለጫዎች እንጂ የልዩነት መንስኤ ሊሆኑ አይገባም
ታህሳስ 27/2014/ኢዜአ/ የኢትዮጵያ ታሪኮች የጋራ ማንነት መገለጫዎች እንጂ የልዩነት መንስኤ ሊሆኑ እንደማይገባ የሰላም ሚኒስቴር ገለጸ።
የሰላም ሚኒስቴር ''ታሪካዊ አበርክቶ ለብሔራዊ መግባባትና የታሪክ ምሁራን ሚና'' በሚል ከአዲስ አበባ ዩኒቨርስቲ ጋር በመተባበር የምክክር መድረክ አዘጋጅቷል።
በምክክር መድረኩ ላይ የሰላም ሚኒስቴር ሚኒስትር ዴኤታ አቶ ታዬ ደንደአ እንዳሉት ታሪኮቻችን የጋራ ማንነታችን መገለጫዎች መሆናቸውን መረዳት ይገባል።
ኢትዮጵያ የበርካታ ታሪኮች ባለቤት መሆኗን ያነሱት ሚኒስትር ዴኤታው በአተረጓጎምና በታሪክ ሽሚያዎች ሳቢያ ታሪኮቻችን የልዩነት መንስኤ ሊሆኑ እንደማይገባ ተናግረዋል፡፡
በታሪክ መቶ ዓመታትን የፈጀ ጦርነት ያካሂዱ የዓለማችን አገራት ቢኖሩም አሁን ላይ በመግባባትና በመነጋገር የታሪክ ቁርሾአቸውን በመተው በብልፅግና ጎዳና ላይ ይገኛሉ፡፡
በእኛ አገርም የታሪክ ሽሚያዎች የሚፈጥሩትን ቁርሾ ለማስተካከል ታሪክ የሚተነተንበትንና የሚተረጎምበትን ሂደት በማስተካከል ረገድ ከዘርፉ ምሁራን ብዙ ስራ እንደሚጠበቅ ጠቁመዋል፡፡
ታሪኮቻችን የመለያያ የቁርሾና የመናቆሪያ መንገዶች የሚሆኑበት ጊዜ ማክተሙን የተናገሩት ሚኒስትር ዲኤታው ለልዩነቶቻችን መሰረት የነበረው ከፋፋይ ስርዓት ተወግዶ አገራዊ መግባባት የተጀመረበት ወቅት ላይ ደርሰናል ብለዋል፡፡
ለአብነትም አሁን ያለው ገዢ ፓርቲ ከተፎካካሪ የፖለቲካ ፓርቲዎች ጋር እያደረገ ያለው ተግባብቶ የመስራት ሂደት ማሳያ መሆኑንም ጠቁመዋል፡፡
ጥናታዊ ጹሁፍ ያቀረቡት ፕሮፌሰር ባህሩ ዘውዴ በበኩላቸው ታሪክን አዛብቶ ማቅረብ ግጭቶች እንዲባባሱ በማድረግ የህዝብ አብሮነት ላይ የሚያጠላው ጥላ ሰፊ ነው።
አንዳንድ የፖለቲካ ፓርቲዎችና አክቲቪስቶች ለራሳቸው ጥቅም ከታሪክ ሰበዞች ውስጥ እየመዘዙ የሚያወጧቸው ትርክቶች ለዚህ ተጠቃሽ ናቸው ብለዋል፡፡
ታሪክ ራሱን የቻለ ትልቅ ሙያ ነው ያሉት ፕሮፌሰሩ ማንም ከመሬት ተነስቶ የሚፅፈው ሳይሆን ሙያዊ ክህሎቱንና ስነ-ምግባሩን ተከትሎ ሊጻፍ እንደሚገባም አስገንዝበዋል፡፡
መንግስት በዘርፉ የሚታዩ ችግሮችን ለማስወገድ እያደረገ ያለው ጥረት ሊበረታታ ይገባልም ብለዋል፡፡
ሌላኛው ጽሁፍ አቅራቢ ረዳት ፕሮፌሰር አበባው አያሌው በበኩላቸው ባለፉት 27 ዓመታት በመንግስት ደረጃ ታሪክን በማዛባት በትምህርት ቤቶች ጨምሮ ሲሰራ መቆየቱን አውስተዋል፡፡
ታሪክን የፖለቲካ መጠቀሚያ ለማድረግ መሞከር ህዝን ከህዝብ ከማለያየትና ቁርሾ ከማስቀረት በስተቀር ምንም ጥቅም አይሰጥም ነው ያሉት፡፡
በምክክር መድረኩ ላይ ምሁራን የፖለቲካ አመራሮች የዩንቨርስቲው ተማሪዎችና ጥሪ የተደረገላቸው እንግዶች ተሳታፊ ሆነዋል፡፡