ቀጥታ፡

በኢትዮጵያ ባሉ በርካታ የኢንቨስትመንት አማራጮች ዳያስፖራዎች በስፋት በመሳተፍ ተጠቃሚ እንዲሆኑ ጥሪ ቀረበ

አዲስ አበባ፣ ታህሳስ 27 ቀን 2014 (ኢዜአ)  በኢትዮጵያ ባሉ በርካታ የኢንቨስትመንት አማራጮች ዳያስፖራዎች በስፋት በመሳተፍ ተጠቃሚ እንዲሆኑ የኢንቨስትመንት ኮሚሽን ጥሪ አቀረበ፡፡

በኢትዮጵያ ያለው የኢንቨስትመንት አማራጭ የሚተዋወቅበት የኤግዚቢሽንና የምክክር መድረክ ከጥር 3 አስከ 6 ቀን 2013 ዓ.ም ይካሄዳል።

የኢትዮጵያ ኢንቨስትመንት ኮሚሽን ኮሚሽነር ሌሊሴ ነሜ፤ መድረኩን በማስመልከት በሰጡት መግለጫ ኢትዮጵያ ዘርፈ ብዙ የኢንቨስትመንት አማራጭና ምቹ የፖሊሲ ማእቀፎች እንዳሏት አብራርተዋል።

በተለይም ዳያስፖራው በረጅም ቆይታ ያካበተውን እውቀትና ሀብት የሚያለማበት ምቹ ሁኔታ መኖሩን አስረድተዋል።

ዳያስፖራዎች የሀገራቸውን እድገትና የኢንቨስትመንት አማራጭ የሚያረጋግጡባቸው መረጃዎች በዌብ ሳይትና በማህበራዊ ትስስር ገፆች መኖራቸውን ጠቁመዋል፡፡

በሎጅስቲክ ሴክተር፣ በማኑፋክቸሪንግ፣ በአግሮ ፕሮሰሲንግ፣ በኢንደስትሪና አይሲቲ ፓርኮች እንዲሁም በጤናው ዘርፍ የኢንቨስትመንት አማራጮች መኖራቸውን ጠቅሰው ዳያስፖራዎች በፈለጉት አማራጭ በመሳተፍ ተጠቃሚ እንዲሆኑ ጥሪ አቅርበዋል።

ሀገራዊውን ጥሪ ተቀብለው  ለመጡትም ሆነ በተለያዩ ምክንያቶች ወደ ሀገራቸው መምጣት ላልቻሉት ዳያስፖራዎች ሀገራዊውን የኢንቨስትመንት አማራጭ ለማስተዋወቅ ዝግጅት መደረጉን የአዲስ አበባ ኢንቨስትመንት ኮሚሽን ኮሚሽነር ግርማ ሰይፉ ተናግረዋል፡፡

ዳያስፖራው ሀገሩን ለመጎብኘት የመጣ ቢሆንም የሚያገኘውን መረጃ ተንተርሶ ለቀጣይ እቅድ እንዲያወጣ መድረኩ ምቹ አጋጣሚ እንደሚፈጥር  ገልጸዋል ፡፡

የኢንቨስትመንት ፎረሙና የምክክር መድረኩ የኢትዮጵያን የኢንቨስትመንት አቅምና መንግስት ለዘርፉ የሰጠውን ትኩረት የሚረዱበትና ከዚህ በፊት ኢንቨስት አድርገው ውጤታማ የሆኑ ኢንቨስተሮች ልምድ  የሚያካፍሉበት መሆኑንም ጠቅሰዋል።

የኢንቨስትመንት ሴክተሩ የተሻለ አፈጻጸም አሳይቷል ያሉት የኢትዮጵያ ኢንቨስትመንት ኮሚሽን ኮሚሽነሯ ሌሊሴ ነሜ፤ በበጀት አመቱ ባለፉት ወራት 1 ነጥብ 34 ቢሊዮን ዶላር ተገኝቷል ብለዋል።

ገቢው ከባለፈው ዓመት ተመሳሳይ ወራት ጋር ሲነፃፀር የ26 በመቶ ብልጫ ማሳየቱን ጠቁመዋል ፡፡

በአማራና አፋር ክልሎች የወደሙ ኢንቨስትመንቶችን ስራ በማስጀመር ሰራተኞችን ወደ ስራ ገበታቸው ለመመለስና አዳዲስ አማራጮችን ለማስፋት እየተሰራ መሆኑንም ኮሚሽነሯ ገልጸዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም