ህገ ወጥ የቁም እንስሳት ንግድ ኢትዮጵያን ገቢ እያሳጣትና የህጋዊ ነጋዴዎችን ስራም ፈታኝ እያደረገው ነው - ኢዜአ አማርኛ
ህገ ወጥ የቁም እንስሳት ንግድ ኢትዮጵያን ገቢ እያሳጣትና የህጋዊ ነጋዴዎችን ስራም ፈታኝ እያደረገው ነው
አዲስ አበባ፣ ታህሳስ 27 ቀን 2014 (ኢዜአ) ህገ ወጥ የቁም እንስሳት ንግድ ኢትዮጵያን ገቢ እያሳጣትና የህጋዊ ነጋዴዎችን ስራም ፈታኝ እያደረገባቸው መሆኑን የቁም እንስሳት ላኪዎች ማህበር ገለጸ።
ኢትዮጵያ በቁም እንስሳት ሃብቷ ከዓለም አገራት የመጀመሪያዎቹ አስር አገራት ተርታ ላይ ብትገኝም በውጭ ምንዛሬ ግኝት ግን የሚፈለገው ደረጃ ላይ አልደረሰችም።
የንግድና ቀጣናዊ ትስስር ሚኒስቴር መረጃ እንደሚያሳየውም ከዘርፉ የሚገኘው ገቢ መጨመር ሲገባው ከጊዜ ወደ ጊዜ እየቀነሰ መጥቷል።
እንደ ምሳሌ ለመጥቀስም በ2004 ዓ.ም ከ200 ሚሊዮን ዶላር በላይ ገቢ የተገኘ ሲሆን በ2013 ዓ.ም ገቢው ወደ 44 ሚሊዮን ብር ዝቅ ማለቱን ያመለክታል።
ለገቢው መቀነስ አንዱ ምክንያት ደግሞ ህገ ወጥ የቁም እንስሳት ንግድ ሆኖ ይጠቀሳል።
የኢትዮጵያ የቁም እንስሳት ላኪዎች ማህበር ፕሬዝዳንት ክብሬ ሙላት፤ ከኢዜአ ጋር ባደረጉት ቆይታ እንዳሉት ህገ ወጥ ነጋዴዎች የህጋዊ ነጋዴዎችን ስራ ፈታኝ እያደረጉት ይገኛሉ።
"የእንስሳቱ ተቀባዮችም ፊታቸውን ወደ ህገ ወጥ ነጋዴዎች ማዞራቸው ትልቅ ፈተና ደቅኗል" ይላሉ።
"የተቀባይ አገሮችን የጥራት ደረጃ ለሟሟላት ከፍተኛ ወጪ ይጠይቃል" ያሉት ፕሬዝዳንቷ ወጪውን ሸፍነን ከህገ ወጥ ነጋዴዎች ጋር በዋጋ መወዳደር አልቻልንም ሲሉ ችግሩን አስረድተዋል።
ዘመናዊ የትራንስፖርት አገልግሎት መኖር የእንስሳትን ጤና ለማስጠበቅ ያለው ፋይዳ ከፍተኛ በመሆኑ ሊታሰብበት እንደሚገባም አጽንኦት ሰጥተዋል።
የእንስሳት ንግድ ከፍተኛ በጀት የሚጠይቅ እንደመሆኑ በቂ የፋይናንስ አቅርቦት መኖር እንደ ሚገባው ጠቅሰው ዘርፉን ለመደገፍ የሚሰጠው ብድርም ሊጨምር ይገባል ብለዋል።
ኢትዮጵያ ከቁም እንስሳት ንግድ የምታገኘውን ገቢ የበለጠ ለማሳደግ "የኮሜርሻል ራንች" ወይም ደግሞ ግዙፍ የእንስሳት እርባታ ማዕከል ሊኖራት ይገባል ብለዋል።