የቋሚ ኮሚቴዎችን አደረጃጀት ለማሻሻል ከጀርመን ፓርላማ ተጨማሪ ልምድ አግኝተናል - ወይዘሮ ሽታዬ ምናለ - ኢዜአ አማርኛ
የቋሚ ኮሚቴዎችን አደረጃጀት ለማሻሻል ከጀርመን ፓርላማ ተጨማሪ ልምድ አግኝተናል - ወይዘሮ ሽታዬ ምናለ
አዲስ አበባ ነሐሴ 21/2010 የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የቋሚ ኮሚቴዎችን አደረጃጀት ለማሻሻል ከጀርመን ፓርላማ ተጨማሪ ልምድ ማግኘቱን የምክር ቤቱ ምክትል አፈ ጉባኤ ወይዘሮ ሽታዬ ምናለ ገለጹ። የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አባላት ከጀርመን ፓርላማ አባላት ጋር በሁለቱ አገሮች ፓርላማ ያለውን ልምድ በተመለከተ ዛሬ በአዲስ አበባ ውይይት አድርገዋል። ኢትዮጵያና ጀርመን የፌዴራሊዝም ስርዓት የሚከተሉ አገሮች ቢሆኑም ጀርመን የተሻለ የፓርላማ አወቃቀርና አሰራር ስርዓት እንዳላት ይታወቃል። የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ምክትል አፈ ጉባኤ ወይዘሮ ሽታዬ ምናለ እንዳሉት፤ ምክር ቤቱ የኅብረተሰቡን ዘርፈ ብዙ ጥያቄዎች ለመመለስና ፍላጎቱን ለማርካት መንግስት የመዋቅር ማሻሻያ እያደረገ ነው። ኅብረተሰቡ በተደጋጋሚ ቅሬታ እያቀረበ ምላሽ ያላገኙ ጥያቄዎችን በአግባቡ ለመፍታት እንዲቻል ምክር ቤቱ ከመንግስት ጋር የስምምነት ሰነድ መፈራረሙን ገልጸዋል። ምክር ቤቱ የተጣለበትን ኃላፊነት በአግባቡ ለመወጣት በሚሰራው አዲስ የቋሚ ኮሚቴዎች አደረጃጀት ማሻሻያ ከጀርመን ፓርላማ የተገኘውን ልምድ በመቀመር አጋዥ መሆኑን ጠቁመዋል። የመከላከያና ደህንነትን ጨምሮ በሌሎች ክፍተት ባለባቸው ቋሚ ኮሚቴዎች ላይ ለምናደርገው ማሻሻያ "ከጀርመን ፓርላማ ያገኘነውን ልምድ በአግባቡ እንጠቀምበታለን" ብለዋል። መንግስት የኅብረተሰቡን ጥያቄ በአግባቡ ተረድቶ ተቋማዊ በሆነ አሰራር ምላሽ ለመስጠት በሚያደርገው እንቅስቃሴ የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ጥብቅ ክትትል ለማድረግ ቁርጠኛ መሆኑንም ገልጸዋል። ምክር ቤቱ በተለያዩ ጉዳዮች ላይ የሚያሳልፋቸው ውሳኔዎችን ለኅብረተሰቡ በቀጥታ ለማድረስ የተለያዩ የኮሙኒኬሽን አግባቦችን እንደሚጠቀም አፈ ጉባኤዋ ገልጸዋል። የጀርመን ፓርላማ አባል ክርስቶፍ ማትሼ በበኩላቸው ኢትዮጵያ የጀመረችው ጤናማ ለውጥ ቀጣይነት እንዲኖረው "ጠንካራ መዋቅራዊ አደረጃጀት መፍጠርና ውይይቶችን ለህዝብ ክፍት ማድረግ ይገባል" ብለዋል። የኢትዮጵያ መንግስት ለጀመረው ማሻሻያ የጀርመን መንግስት ማንኛውንም ድጋፍ ለማድረግ እና ልምድ ለማካፈል ዝግጁ መሆኑን ጠቁመዋል። የፓርላማ አወቃቀርና አደረጃጀት ከአገራቷ ወግ፣ ባህልና የአኗኗር ዘይቤ አኳያ መቃኘት እንዳለበት ገልጸው፤ ኢትዮጵያም ይሄንን ልምድ ማጎልበት እንዳለባት ጠቁመዋል።