ቀጥታ፡

የአምባሳደር ካሳ ከበደ አስከሬን በቦሌ ዓለም አቀፍ አውሮፕላን ማረፊያ አቀባበል ተደረገለት

ታህሳስ 27 ቀን 2014 (ኢዜአ)የአምባሳደር ካሳ ከበደ (ዶክተር) አስከሬን በቦሌ ዓለም አቀፍ አውሮፕላን ሲደርስ የቀድሞ የስራ ባልደረቦቻቸው እና ወዳጅ ዘመዶች ተገኝተዋል።

በቀድሞው የደርግ ወታደራዊ መንግስት ከፍተኛ የመንግስት የስራ ኃላፊ የነበሩት አምባሳደር ዶክተር ካሳ ከበደ በግርማዊ ቀዳማዊ ኃይለስላሴ የመንግስት አስተዳደር ዘመን ከፍተኛ ባለስልጣን ከነበሩት ከአባታቸው ደጃዝማች ከበደ ተሰማ እና ከእናታቸው ወይዘሮ እመት ይታጠቁ ኪዳኔ በ1934 ዓ/ም በአዲስ አበባ ከተማ ነበር የተወለዱት።

አምባሳደር ካሳ ከበደ (ዶ/ር) በተለያዩ ኃላፊነቶች ሀገራቸውን ያገለገሉ ሲሆኑ ትምህታቸውንም በአዲስ አበባ ተፈሪ መኮንን ትምህርት ቤት፤ እንዲሁም በታዋቂው የእስራኤሉ ህብሪው ዩኒቨርሲቲ የስነ ማህበረሰብ ጥናት ትምህርት ክፍል ከፍተኛ ትምህርታቸውን ተከታትለዋል።

ትምህርታቸውን ተከታትለው ካጠናቀቁ በኋላም በአምባሳደርነት፣ ሚኒስትርነት እና ባለሙያነት ባሉ ከፍተኛ የስራ ኃላፊነቶች ሀገራቸውን በማገልገል ጉልህ ሚና አበርክተዋል።

የደርግ ወታደራዊው መንግስት ከመንበረ ስልጣን ከተወገደ በኋላም በስደት በእስራኤል፣በስዊዘርላንድና በተለይም በዩናይትድ ስቴትስ ከሰላሳ ዓመታት በላይ አሳልፈዋል።

የአምባሳደር ካሳ ከበደ አስከሬን ግንፍሌ አካባቢ በሚኖሩት እህታቸው ወይዘሮ አሰገደች ከበደ መኖሪያ ቤት በኢትዮጵያ የኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተክርስቲያን ስርዓትና ቀኖና መሰረት ፆለትና ፍትሃት መርሃ ግብር እየተካሄደ ሲሆን ከሰዓታት በኋላ በቅድስት ስላሴ ካቴደራል ቤተክርስቲያን ስርዓተ ቀብራቸው ይፈጸማል።

አምባሳደር ካሳ (ዶ/ር) የአንድ ወንድ እና ሁለት ሴት ልጆች አባት ነበሩ።

አምባሳደር ካሣ ከበደ (ዶ/ር) የካቲት 18/1934 በተወለዱ በ80 ዓመታቸው በህክምና ሲረዱ ቆይተው ታህሳስ 16/2014 ዓ/ም ከዚህ ዓለም በሞት ተለይተዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም