በኢትዮጵያ ላይ የሚነዙት የሐሰት ትርክቶች መሬት ላይ ካለው የአገሪቱ ሁኔታ ጋር ፍጹም የተቃረኑ ናቸው - ኢዜአ አማርኛ
በኢትዮጵያ ላይ የሚነዙት የሐሰት ትርክቶች መሬት ላይ ካለው የአገሪቱ ሁኔታ ጋር ፍጹም የተቃረኑ ናቸው
ታህሳስ26/2014/ኢዜአ/ በኢትዮጵያ ላይ የሚነዙት የሐሰት ትርክቶች ወደ አገር ቤት መጥተን ካገኘነው የአገሪቱ ሁኔታ ጋር ፍጹም የተቃረኑ ናቸው ሲሉ ከሊባኖስ-ቤሩት የመጡ ኢትዮጵያውያን ገለጹ።
ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ አህመድ ያደረጉትን ጥሪ ተከትሎ በተለያዩ የዓለም አገራት የሚኖሩ ኢትዮጵያውያን፣ ትውልደ ኢትዮጵያውያንና የኢትዮጵያ ወዳጆች ወደ አገር ቤት እየገቡ ነው።
ወደ አገር ቤት ከገቡት ከእነዚህ የዳያስፖራ አባላት መካከል በሊባኖስ ቤሩት ከ18 ዓመታት በላይ ነዋሪ የሆኑት ኢትዮጵያዊያን በዚህ ጊዜ ወደ አገራቸው በመምጣታቸው የተሰማቸውን ደስታ ይገልጻሉ።
በሊባኖስ-ቤሩት ነዋሪ የሆኑት ትዕግስት አራጋውና ሃና መገርሳ አገራቸው ገብተው ተዘዋውረው ያለውን ሁኔታ እንዳጤኑ ገልጸው በውጭው ዓለም በኢትዮጵያ ላይ የሚነዙት የሐሰት ትርክቶች መሬት ላይ ካለው የአገሪቱ እውነታ ጋር የተቃረኑ መሆናቸውን ነው የተናገሩት።
በተለይም የዓለም አቀፍ መገናኛ ብዙሃን የኢትዮጵያን ወቅታዊ ጉዳይ በተመለከተ የሚያሰራጩት ያልተጣራ መረጃ ሕዝቦች እንዲሸበሩ የሚያደርግ እንደሆንም ገልጸዋል።
ይሁንና ወደ አገር ቤት ሲመጡ የተመለከቱት የከተማዋ ነባራዊ ሁኔታና የሕዝቡ ሰላማዊ እንቅስቃሴ ከሚነዙት ሃሰተኛ ወሬዎች ጋር የተራራቁ ሆነው ማግኘታቸው እንዳስደሰታቸውም ተናግረዋል።
በከተማዋ ካለው የሰላም ሁኔታ ባሻገር የህዝቡ ትብብር፣ የከተማዋ ውበትና የልማት ሥራዎች የሚያስደስት ነው ሲሉም ተናግረዋል።
በዚህ ወቅት ለዲያስፖራው የተደረገው ጥሪ ኢትዮጵያውያን ከመቼውም ጊዜ በላይ አንድነታቸውን እንዲያጠናክሩ ይበልጥ እድል የሚፈጥር ነውም ብለዋል።
በቀጣይም የኢትዮጵያን ወቅታዊ የፖለቲካ ሁኔታ ለዓለም አቀፉ ኅብረተሰብ የማሳወቅ ሥራ ላይ ይበልጥ በመሳተፍ የዜግነት ግዴታቸውን እንደሚወጡ አረጋግጠዋል።