ቀጥታ፡

ኢትዮጵያ ውጭ በሚኖሩ ምሁራኖቿ እንድትታገዝ መንግሥት በጉዳዩ ዙሪያ በትኩረት ሊሰራ ይገባል

አዲስ  አበባ፤ ታህሳስ 26 /2014 (ኢዜአ)  የዳያስፖራው ተሳትፎ አሁን ካለው ይልቅ እንዲሰፋና ኢትዮጵያ ውጭ በሚኖሩ ምሁራኖቿ እንድትታገዝ መንግሥት በጉዳዩ ዙሪያ በትኩረት ሊሰራ ይገባል ሲሉ የግሎባል ኤይድ በኢትዮጵያ መሥራችና በካናዳ የኢመርጀንሲ ሐኪም ዶክተር ጌታቸው ደመም ገለጹ።

ኢትዮጵያ በውስጥና በውጭ የተከፈተባትን ዘርፈ ብዙ ትግሎችና ፈተናዎች ተቋቁማ ለማለፍ ሰፊ ርብርብ የሚያሻው ጊዜ ላይ ትገኛለች።

በተለይ በውጭ የሚኖሩ ኢትዮጵያዊያንና ትውልደ ኢትዮያዊያን ዳያስፖራዎች ''ከአገር በፊት እኔን'' በሚል ስሜት በዓለም አደባባይ ወጥተው የኢትዮጵያ እውነታ ከማስረዳት እስከ የ# በቃ ወይም የ # NO MORE ንቅናቄ ድረስ ሰፊ ተሳትፎ እያደረጉ ይገኛሉ።

በቅርቡም ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ አህመድ ባቀረቡት ጥሪ መሰረት በርካታ ኢትዮጵያዊያንና ትውልደ ኢትዮጵያዊያን ወደ አገራቸው በመምጣት አለኝታነታቸውን እያረጋገጡ ነው።

የግሎባል ኤይድ በኢትዮጵያ መሥራችና በካናዳ የኢመርጀንሲ ሐኪም ዶክተር ጌታቸው ደመም ከኢዜአ ጋር በበይነ መረብ በነበራቸው ቆይታ አሁን በውጭ በሚኖሩት ኢትዮጵያዊያንና ትውልደ ኢትዮጵያዊያን ዳያስፖራዎች የተጀመረው ንቅናቄ በይበልጥ ተጠናክሮ መቀጠል አለበት ብለዋል።

ዳያስፖራው በአሁኑ ወቅት እያደረገ ያለውን እንቅስቃሴ በራሱ ተነሳሽነት እያደረገ ያለ መሆኑን በማንሳት ከዚህ ይበልጥ ሚና እንዲኖራቸው ግን መንግሥት በጉዳዩ ላይ ትኩረት ሰጥቶ ሊሰራ እንደሚገባ ነው የተናገሩት።

በተለይ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር በዓለም ላይ የኢትዮጵያ ምሁራን የት ይገኛሉ? የሚል ፍለጋ በማድረግ ምሁራኑ አገራቸውን የሚያግዙበትን መንገድ ማመቻቸት እንደሚገባ ገልጸዋል።

''ኢትዮጵያ የጠራችንና የምትፈልገን አሁን ነው'' ያሉት ዶክተር ጌታቸው፤ አገር የልጆቿን ድጋፍ ስትፈልግ አለን ልንላት ይገባል ብለዋል።

በሙያቸው "አንቱ" የተባሉ ትውልደ ኢትዮጵያዊያን በየአገሩ ያሉ መሆኑን በማንሳት እነሱን ባላቸው እውቀትና ችሎታ አገራቸውን እንዲያግዙ ማድረግ ይጠበቃል ብለዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም