የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቴአትር በአሸባሪው ህወሃት ጉዳት በደረሰባቸው አካባቢዎች የትዕይንተ ጥበባት ዝግጅት ሊያቀርብ ነው - ኢዜአ አማርኛ
የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቴአትር በአሸባሪው ህወሃት ጉዳት በደረሰባቸው አካባቢዎች የትዕይንተ ጥበባት ዝግጅት ሊያቀርብ ነው
ታህሳስ 26/2014/ኢዜአ/ የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቴአትር በአሸባሪው ህወሃት ጉዳት በደረሰባቸው አካባቢዎች የትዕይንተ ጥበባት ዝግጅት እንደሚያቀርብ አስታወቀ።
"ጥበብ ለብሔራዊ አንድነት" በሚል መሪ ሐሳብ የሙዚቃ ፣ የቴአትር ፣ የግጥምና የመነባንብ ዝግጅት ትናንት ማምሻውን በብሔራዊ ቴአትር ለመከላከያ ሰራዊት አባላት ቀርቧል።
በመድረኩ ጉዳት በደረሰባቸው አካባቢዎች ለማቅረብ ከተዘጋጁ ትይንተ ጥበባት መካከል የተወሰኑት በማሳያነት ቀርበዋል፡፡
በቴአትር ቤቱ የቴአትር አዘጋጅ የሆነው አርቲስት ሳሙኤል ተስፋዬ ትዕይንተ ጥበቡ የተዘጋጀው በአሸባሪው ህወሃት ወረራ ጉዳት የደረሰባቸውን ዜጎች በስነ-ልቦና ለማነቃቃት መሆኑን ተናግሯል፡፡
በጦርነት ወቅት ለተከሰቱ ሰብዓዊና ቁሳዊ ጉዳቶች የሚሰጠውን ትኩረት ያህል ጉዳት የደረሰባቸውን ዜጎች ስነ-ልቦና ለማነቃቃት መስራት እንደሚገባም ነው የገለጸው፡፡
ትይንተ ጥበቡም ይህን ታሳቢ በማድረግ ተዘጋጅቷል ነው ያለው፡፡
በመርሃ ግብሩ ላይ የተገኙት ረዳት ፕሮፌሰር ነብዩ ባዬ በበኩላቸው ጥበብ የሀገር ፍቅር ስሜትን ለማነቃቃትና የተጎዳ ስነ-ልቦናን ለመጠገን ያለው አስተዋጽኦ ከፍተኛ መሆኑን ተናግረዋል፡፡
ከዚህ አኳያ ቴአትር ቤቱ የኪነ-ጥበብ ሥራዎችን ተደራሽ የማድረጉን ስራ አጠናክሮ እንዲቀጥል ጠይቀዋል፡፡
የሀገር መከላከያ ሠራዊት የሕዝብ ግንኙነት ኃላፊ ኮሎኔል ጌትነት አዳነ፤ የኪነ ጥበብ ባለሙያዎች ሰራዊቱ የተሰጠውን ግዳጅ በድል እንዲወጣ ጉልህ ሚና ማበርከታቸውን ገልጸዋል፡፡
የኪነ-ጥበብ ሥራዎችን በመጠቀም ጉዳት የደረሰባቸውን ወገኖች ስነ-ልቦና ማነቃቃት እንደሚገባም ጥሪ አቅርበዋል፡፡
"የኪነ-ጥበብ ሥራዎች በድል ብርሃን እንድንጓዝ አግዘውናል፤ አሁንም ኪነ-ጥበብን ለስነ-ልቦና መነቃቃት መጠቀም ይገባል" ያሉት ደግሞ የኢፌዴሪ ባህልና ስፖርት ሚኒስትር ድኤታ አምባሳደር መስፍን ቸርነት ናቸው፡፡
ለዚህ ደግሞ ሚኒስቴር መሥሪያ ቤቱ የሚጠበቅበትን ድጋፍ ያደርጋል ነው ያሉት፡፡