ከሰብአዊ ድጋፍ ባለፈ በዘላቂነት የምንቋቋምበት እገዛ እንፈልጋለን - ኢዜአ አማርኛ
ከሰብአዊ ድጋፍ ባለፈ በዘላቂነት የምንቋቋምበት እገዛ እንፈልጋለን
ደሴ፤ ታህሳስ 26/2014 (ኢዜአ) ከሚደረግላችው የዕለት ደራሽ ሰብአዊ ድጋፍ ባለፈ በዘላቂነት ለመቋቋም እገዛ እንደሚያስፈልጋቸው በደቡብ ወሎ ዞንና አካባቢው በአሸባሪው የህወሃት ቡድን የተፈናቀሉ ወገኖች ተናገሩ።
በዞኑ የሐይቅ ከተማ ነዋሪ አቶ አሊ ሰይድ ለኢዜአ እንዳሉት፤ አሸባሪው ህወሓት በከተማዋ በወረራ በቆየባቸው ጊዜያት የንጹሀን ዜጎችን ህይወት ከመቅጠፉም ባለፈ የንብረት ዝርፊያና ውድመት ፈጽሟል።
በሽብር ቡድኑ ድርጊት ምክንያት ከአራት ቤተሰባቸው ጋር ለችግር ቢዳረጉም፥ በአሁኑ ወቅት የምግብ ድጋፍ እየተደረገላቸው መሆኑን አንስተው በዘላቂነት ለመቋቋም እገዛ እንደሚያስፈልጋቸው ተናግረዋል።
አሸባሪው ህወሓት በከፈተው ጦርነት ስድስት የቤተሰብ አባላትን ይዘው ለከፋ ችግር ተዳርገው መቆየታቸውን የገለጹት ደግሞ የደሴ ከተማ ነዋሪ አቶ ሰይድ ሁሴን ናቸው።
በአሁኑ ወቅት መንግስት ተቋማትንና ሕብረተሰቡን በማስተባባር በጦርነቱ ምክንያት የተቸገሩትን ለመደገፍ እያደረገ ያለውን ጥረት አድንቀዋል።
የደቡብ ወሎ ዞን አደጋ መከላከልና ምግብ ዋስትና ተጠሪ ጽህፈት ቤት ኃላፊ አቶ መሳይ ማሩ በበኩላቸው፤ ለችግር ለተጋለጡ ወገኖች ድጋፍ እየተደረገ ነው ብለዋል።
በደቡብ ወሎ፣ ደሴ ከተማ እና አካባቢዋ በሽብር ቡድኑ ለተፈናቀሉና ለተቸገሩ 3 ነጥብ 5 ሚሊዮን ዜጎች ከ428 ሺህ ኩንታል በላይ የምግብ እህል ያስፈልጋል ነው ያሉት።
"እስካሁን በተደረገው ጥረት ከ55 ሺህ ኩንታል በላይ ቀርቦ፤ በደላንታ፣ ወገል ጤና፣ ወረባቦ፣ ተሁለደሬ፣ ሃይቅ፣ ኮምቦልቻ፣ ጃማ፣ ወርኢሉና ሌሎች ወረዳዎች የከፋ ችግር ላለባቸው ከ233 ሺህ ለሚበልጡ ዜጎች ድጋፍ ተደርጓል" ብለዋል።
ቀሪውን ምግብ በፍጥነት አሰባስቦ ለተጎጂዎች እንዲከፋፈል ከሚመለከታቸው አካላት ጋር በቅንጅት እየተሰራ መሆኑን ተናግረዋል።
የደቡብ ወሎ ዞን ዋና አስተዳዳሪ አቶ አብዱ ሁሴን ከዕለት እርዳታ ባሻገር ዜጎችን በዘላቂነት እንዲቋቋሙ ከዞን እስከ ፌደራል በኮሚቴ እየተሰራ መሆኑን አስታውቀዋል።
በተለይ የጤናና የትምህርት ተቋማትን በፍጥነት በመጠገን በከፊልም ቢሆን አገልግሎት እንዲሰጡ እየተደረገ መሆኑን ነው አቶ አብዱ የጠቆሙት።
ዜጎች ከደረሰባቸው የስነ ልቦና ጫና ተላቀው መልሰው እንዲቋቋሙና በሙሉ አቅማቸው ወደቀድሞ ሥራቸው እንዲመለሱም አስፈላጊው እገዛና ድጋፍ እንደሚደረግ ገልጸዋል።