ቀጥታ፡

የኢትዮጵያ ወጣቶች አገራቸውን ከውስጥና ከውጭ ጠላቶች ለመጠበቅ ያላቸው ጊዜ 'አሁን' ነው

አዲስ  አበባ፤ ታህሳስ 26 /2014 (ኢዜአ)   የኢትዮጵያ ወጣቶች አገራቸውን ከውስጥና ከውጭ ጠላቶች ለመጠበቅ ያላቸው ጊዜ 'አሁን' ነው ሲል ደቡብ አፍሪካዊው የማኅበረሰብ ንቅናቄ መሪ ሎንታታ ላክስ ተናገረ።

ኢትዮጵያዊያን ወጣቶች "በጋራ የምትቆሙበት ሠዓት አሁን ነው፣ እንደ አሁን አይነት ሌላ ጊዜ የላችሁም"

የ34 ዓመቱ ወጣት ሎንታታ ላክስ በደቡብ አፍሪካ ከጊዜ ወደ ጊዜ ተሰሚነቱ እየጨመረ የመጣ የማኅበረሰብ ንቅናቄ መሪ ነው።

ወጣቱ ላክስ በሚኖርበት ስዌቶ "ስዌቶ ፓርላማ" የተሰኘ የወጣቶች ኅብረት በመፍጠር ማኅበራዊ ፍትህ ለማስፈን ሰፊ ዘመቻ እያካሄደ ይገኛል።

በደቡብ አፍሪካ በተካሄደው #nomore የተቃውሞ ሠልፍ በመሳተፍ ድጋፉን የሰጠ፣ አፍሪካዊያን ኢትዮጵያን እንዲደግፉም ጥሪ ያቀረበ የኢትዮጵያ ወዳጅ ነው ወጣቱ ሉንታታ ላክስ።

ወደ ኢትዮጵያ የመጣው ይህ ወጣት ትናንት የእንጦጦ ፓርክን ከጎበኘ በኋላ በውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር አማካኝነት የእራት ግብዣ ተደርጎለታል።

የሚኒስቴሩ ቃል አቀባይ አምባሳደር ዲና ሙፍቲ፤ ላክስ ከታላቋ የኔልሰን ማንዴላ አገር ደቡብ አፍሪካ የመጣ መሆኑ ብቻ ሳይሆን ኢትዮጵያ በልቡ ውስጥ እንዳለች ተግባራቱ ይመሰክራሉ ብለዋል።

ወጣቱ በኢትዮጵያ ያለውን ለውጥ በመደገፍ ወጣቶች ለአገራቸው ነፃነትና ሠላም እንዲታገሉ መልዕክት ለማስተላለፍ መምጣቱንም ተናግረዋል።

ደቡብ አፍሪካዊው የማኅበረሰብ ንቅናቄ መሪ ሎንታታ ላክስ በበኩሉ የኢትዮጵያ ወጣቶች አገራቸውን ለመጠበቅ ያላቸው ጊዜ 'አሁን ብቻ ነው' ብሏል።

ኢትዮጵያን ለማጥፋት ከተነሱ የውስጥና የውጭ ጠላቶች አገራቸውን ለመጠበቅ በጋራ ሊቆሙ ይገባል ሲል ተናግሯል።

የፐብሊክ ዲፕሎማሲ አባል ዶክተር ወዳጄነህ ማህረነ በበኩላቸው የወጣቱ ወደ ኢትዮጵያ መምጣት የሁለቱ አገራት ወጣቶች ልምድ እንዲለዋወጡ እንደሚያስችል ገልጸዋል።

"ከደቡብ አፍሪካ የመጡ ወንድሞቻችንን በማግኘታችን በጣም ደስ ብሎኛል፡ በእውቀት የተሞሉ፣ በጣም የነቁ ሰዎች ናቸው በአገራቸው ደግሞ ብዙ ስራ እየሰሩ ያሉ ናቸው፡ የእኛ ወጣቶች ደግሞ ከእነሱ ብዙ ሊማሩ ይችላሉ" ብለዋል። 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም