ቀጥታ፡

የኢትዮጵያ ሕዝብ ለሀገራዊ የምክክር ሂደት ውጤታማነት የነቃ ተሳትፎ እንዲያደርግ ጥሪ ቀረበ

ታህሳስ 25 ቀን 2014 (ኢዜአ) የሀገራዊ ምክክር ሂደት ውጤታማ እንዲሆን ሁሉም የኢትዮጵያ ሕዝብ በንቃት እንዲሳተፍ የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ጥሪ አቀረበ።

የምክር ቤቱ አፈ ጉባኤ ታገሰ ጫፎ፤ የምክክር ኮሚሽኑ አስፈላጊነትና የእጩ ኮሚሽነሮች ጥቆማን አስመልክቶ መግለጫ ሰጥቷል።

በመግለጫቸውም የሀገራዊ ምክክር ኮሚሽኑ የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤትን ጭምሮ የተለያዩ አካላት ከተወያዩበት በኋላ መፅደቁን አስታውሰዋል።

ከሁሉም በላይ የሀገራዊ ምክክር ኮሚሽኑ አስፈላጊነት ላይ መላው የኢትዮጵያ ሕዝብ ብዥታ ሊኖርበት አይገባውም ያሉት አፈ ጉባኤው፤ ምክክሩ የኢትዮጵያን ጥንታዊ እሴቶች ማስቀጠልን ታሳቢ ያደረገ መሆኑን ገልጸዋል።

የምክክር ሂደቱ አላማ በኢትዮጵያውያን መካከል የሚስተዋሉ ልዩነቶችን ማጥበብና ሀገራዊ አንድነትን ማጠናከር መሆኑን ጠቅሰዋል።

ከውስጥም ሆነ ከውጭ በኢትዮጵያ ላይ የተሸረበውን ሴራ ለማክሸፍም የኢትዮጵያውያን መመካከር ወሳኝ መሆኑን ጠቅሰው ለስኬታማነቱ የዜጎች የነቃ ተሳትፎ እንዲኖር ጠይቀዋል።

የሌሎች ሀገራት ተሞክሮ የሚያሳየውም ሀገራዊ ምክክር የተራራቁ የሕዝቦች ፍላጎቶችን ለማቀራረብ የሚረዳ ነው ብለዋል።

''ሂደቱ በታሪካችን ትልልቅና ጠቃሚ ውሳኔዎች እንዲወሰኑ ሊያደርግ የሚችል ነው'' ሲሉም አፈ ጉባኤው ገልጸዋል።

ሀገራዊ ምክክሩን ከጦርነቱ ወቅታዊ ሁኔታና ከአሸባሪ ድርጅቶች ጋር የሚያገናኙ አካላት ትክክል አለመሆናቸውን አብራርተዋል።

መንግስት በጦርነቱ የተፈናቀሉ ወገኖችን የማቋቋም ስራውን ይቀጥላል፤ ኮሚሽኑ ችግሮችን በውይይት የመፍታት ስራውን የሚያከናውን ይሆናል ነው ያሉት።

የምክክር ኮሚሽኑን የሚመሩ የ11 ኮሚሽነሮች ጥቆማ ከዛሬ ጀምሮ እስከ ጥር 6 ቀን 2014 ዓ.ም ድረስ እንደሚቆይ ጠቅሰዋል።

ኢትዮጵያውያን እጩ ሲጠቁሙ የስራ ብቃትና ልምድን፣ በህዝብ ዘንድ ያላቸውን ተቀባይነት፣ ለሀገር ያበረከቱትን አስተዋጽኦ፣ በሀገራዊ አንድነት ያላቸውን አቋም፣ የስነ ምግባር ሁኔታና ሌሎች አበርክቶዎችን ታሳቢ ማድረግ አለባቸው ብለዋል አፈጉባኤው።

ኢትዮጵያን እናልማ፣እንገንባ፣እንዘጋጅ 

‼️

ሀገርን በዘላቂነት እናልማ

‼️

የፈረሰውን አብልጠን እንገንባ

‼️

ለማንኛውም ፈተና እንዘጋጅ

‼️
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም