የዳያስፖራ አባላት ለሰራዊቱ ድጋፍ የሚያደርጉበት የገቢ ማሰባሰቢያ ሰርተፊኬት ተዘጋጀ - ኢዜአ አማርኛ
የዳያስፖራ አባላት ለሰራዊቱ ድጋፍ የሚያደርጉበት የገቢ ማሰባሰቢያ ሰርተፊኬት ተዘጋጀ
ታህሳስ 25 ቀን 2014 (ኢዜአ)የዳያስፖራ አባላት ለሰራዊቱ ያላቸውን ድጋፍ የሚገልጹበት የገቢ ማሰባሰቢያ ሰርተፊኬት መዘጋጀቱን የአገር መከላከያ ሚኒስቴር ገለጸ።
ዳያስፖራዎችና የኢትዮጵያ ወዳጆች የገና በዓልን አገር ቤት ተገኝተው እንዲያከብሩ ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር ዐቢይ አህመድ ባደረጉት ጥሪ መሰረት በርካቶች በመግባት ላይ ይገኛሉ።
የጠቅላይ ሚኒስትሩን ጥሪ ተቀብለው የተገኙ ዳያስፖራዎች ለሀገር መከላከያ ሰራዊት ያላቸውን ድጋፍ የሚገልጹበት የገቢ ማሰባሰቢያ ሰርተፊኬት መዘጋጀቱን የመከላከያ ሚኒስትር ዴኤታ ማርታ ሉዊጂ ገልጸዋል።
የድጋፍ ሰርተፊኬቱ ከ500 እስከ 10 ሺህ ድረስ በዶላር፣ በዩሮ እና በፓውንድ ዳያስፖራው አበርክቶውን እንዲያደርግ የተዘጋጀ መሆኑን ተናግረዋል።
የገቢ ማሰባሰቢያው ዳያስፖራው ለሰራዊቱ ያለውን ድጋፍ እንዲገልጽ እንዲሁም የሰራዊቱን አቅም ለመገንባት እንዲያስችል መዘጋጀቱን ጠቅሰዋል።
በዚህ የታሪክ አጋጣሚ ዳያስፖራዎች በኢትዮጵያ አሻራቸውን እንዲያሳርፉ መልካም አጋጣሚ የሚፈጥር መሆኑንም ገልጸዋል።
የገቢ ማሰባሰቢያ ሰርተፊኬቱን በኢትዮጵያ አየር መንገድ መግቢያና መውጫ ላይ እንዲሁም በሆቴሎች እና በመከላከያ ሚኒስቴር በአካል በመቅረብ ማግኘት እንደሚችሉ ሚኒስትር ዴኤታዋ ጠቁመዋል።
የኢትዮጵያ ቱሪዝምና ሆቴል ማርኬቲንግ ማህበር ፕሬዚዳንት ጌታሁን አለሙ፤ የገቢ ማሰባሰቢያው ኢትዮጵያ የልጆቿን ድጋፍ በምትሻበት ወቅት አበርክቶ በማድረግ የዚህ ታሪክ አካል ለመሆን እድል እንደሚፈጥር ነው የተናገሩት።
በአሜሪካ፣ ካናዳ እና እንግሊዝ በሚኖሩ ኢትዮጵያውያንና ትውልደ ኢትዮጵያውያን አስተባባሪነት 300 ሺህ ብር የሚገመት የገቢ ማሰባሰቢያ ሳጥን ድጋፍ የተደረገ ሲሆን በኢትዮጵያ አየር መንገድ መግቢያና መውጫ እንደሚቀመጥ ተገልጿል።
በተጨማሪም በ12 የአውሮፓ ሀገራት የሚኖሩ ኢትዮጵያውያንና ትውልደ ኢትዮጵያውያንን ያቀፈ "ዲፌንድ ኢትዮጵያ" የተሰኘ ማህበር በርካታ የህክምና መርጃ መሳሪያዎችን አበርክቷል።
ኢትዮጵያን እናልማ፣እንገንባ፣እንዘጋጅ
ሀገርን በዘላቂነት እናልማ
የፈረሰውን አብልጠን እንገንባ
ለማንኛውም ፈተና እንዘጋጅ