ቀጥታ፡

ለፀጥታ ኃይሉ 3 ሚሊዮን ብር የሚገመቱ ምግብ ነክ ቁሶች ድጋፍ ተደረገ

ታህሳስ 25 ቀን 2014 (ኢዜአ) የጎንደር ከተማ ነዋሪዎች በምዕራብ ግንባር ለሚገኘው የፀጥታ ኃይል 3 ሚሊዮን የሚገመቱ ምግብ ነክ ቁሶች ዛሬ ድጋፍ አደረጉ።

የጎንደር ከተማ ትምህርት መምሪያ ምክትል ኃላፊ አቶ ነፃነት መንግስቴ በገንዳ ውሃ ከተማ በተካሄደው የድጋፍ ርክክብ ላይ እንዳሉት፤በተባበረ ክንድ የሽብር ቡድኑን እስከ መጨረሻው ድረስ ማጥፋት የመላው ኢትዮጵያውያን ሃላፊነት ነው።

ለዚህም በየግንባሩ ለሚገኘው የፀጥታ ሃይል ያልተቋረጠ የሎጅስቲክስ ድጋፍ ማድረግ እንደሚገባ አመልክተዋል።

ድጋፉ ከመምህራንና ተማሪዎች ጭምሮ ከተለያዩ የከተማዋ ነዋሪዎች በተሰበሰበ 3 ሚሊዮን ብር የተዘጋጀ መሆኑን ጠቅሰው፤ከዚህ በፊትም በደባርቅ፣በወሎና ደብረ ታቦር ግንባር ድጋፍ መደረጉን አስታውሰዋል።

በቀጣይም ድጋፉ እንደሚጠናከር አስታውቀዋል።

የምዕራብ ጎንደር ዞን ምክትል አስተዳዳሪና የሎጅስቲክ አስተባባሪ ሲስተር ክሽን ወልዴ በበኩላቸው፤የዚህ ግንባር መጠናከር ለሌሎች አካባቢዎች ሰላም መረጋገጥ ከፍተኛ ሚና አለው ብለዋል።

ከከተማ አስተዳደሩ ነዋሪዎች የተደረገው ድጋፍ ለሃገርና ህዝብ ሲሉ በግንባር እየተዋደቁ ለሚገኙ ሃይሎች ተጨማሪ አቅም እንደሚሆን ገልጸዋል።

የሽብር ቡድኑን እኩይ ሴራ እስከ መጨረሻው ለማክሰም ለፀጥታ ሃይሉ እየተደረገ ያለው ሁለንተናዊ ድጋፍም ተጠናክሮ መቀጠል እንዳለበትም አሳስበዋል።

ኢትዮጵያን እናልማ፣እንገንባ፣እንዘጋጅ

‼️

ሀገርን በዘላቂነት እናልማ

‼️

የፈረሰውን አብልጠን እንገንባ

‼️

ለማንኛውም ፈተና እንዘጋጅ

‼️
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም