የምግብ ዘይት አምራቾች ማህበር ሊመሰረት ነው - ኢዜአ አማርኛ
የምግብ ዘይት አምራቾች ማህበር ሊመሰረት ነው
አዲስ አበባ ግንቦት 9/2010 ኢትዮጵያ ውስጥ በምግብ ዘይት ኢንዱስትሪው ላይ ከማምረትና ከግብይት ጋር በተያያዘ እያጋጠሙ ያሉትን ችግሮች በዘላቂነት ለመፍታት የሚደረገውን ጥረት ያግዛል ተብሎ የታመነበት የዘርፉ አምራቾች ማህበር ሊቋቋም ነው። የአገሪቷ ምግብ ዘይት ኢንዱስትሪ ዘርፍ የጥሬ እቃና ቴክኖሎጂ ግብዓት፣ የማኔጅመንት፣ የሰው ኃይልና የመለዋወጫ እቃዎች አቅርቦት እንደዚሁም የግብይት ስርዓት ችግሮች አሉበት። ማህበሩን ለማቋቋም በተረቀቀው የመተዳደሪያ ደንብ ላይ ለመወያየት ዛሬ በተጠራው ስብሰባ ላይ በምግብ፣ መጠጥና ፋርማሲዩቲካል ኢንዱስትሪ ልማት ኢንስቲትዩት የቅባት እህሎች ፕሮሰሲንግ ዳይሬክተር አቶ ሃብታሙ ታዬ እንደተናገሩት የማህበሩ መቋቋም በዘርፉ የሚስተዋሉትን ችግሮች ለመፍታት ቁልፍ ሚና ይጫወታል። በመላው አገሪቷ የሚገኙ የምግብ ዘይት አምራቾች አባል እንደሚሆኑበት የሚጠበቀው ይህ ማህበር፤ የአባላቶቹን ጥቅም ከማስጠበቅ ባሻገር በዘርፉ የሚታዩትን ችግሮች በመፍታት አገራዊ ፋይዳም እንደሚኖረው ነው ዳይሬክተሩ የገለጹት። በስብሰባው ላይ የቅቤ ለምኔ ዘይት ፋብሪካ ዋና ስራ አስኪያጅና ባለቤት አቶ ውዱ ሀሰን ኑርዬ በአገር አቀፍ ደረጃ የሚቋቋመው ይህ ማህበር ከሚመለከታቸው የመንግስትት አካላት ጋር በመመካከር በዘርፉ ለሚስተዋሉ ችግሮች መፍትሄ ለማፈላለግ ያስችላል ብለዋል። "ከዘይት ምርት ጥራት ጋር በተያያዘ እየተነሱ ላሉት ችግሮች ተጠያቂ የሚሆኑት ህጋዊ ያልሆኑ፣ የደረጃ መዳቢ መስፈርትን ያላሟሉና የተስማሚነት ምዘና ማረጋገጫ የሌላቸው በድብቅ የሚንቀሳቀሱ የዘይት አምራቾች ናቸው" ሲሉም አቶ ውዱ ገልጸዋል። ይህም በህጋዊ ፍቃድ በሚቀርቡት የምግብ ዘይት ምርቶች ላይ ተጠቃሚው እምነት እንዲያጣ እያደረገው ነው ብለዋል። የአዲስ ምግብ ዘይት ማምረቻ ባለቤት አቶ አዲስ ኢንድሪስ በበኩላቸው በአነስተኛ የምግብ ዘይት ኢንዱስትሪ ውስጥ እየተጠቀሙበት ያለው ማሽን የቆየ ነው፤ ይህም ጥራት ያለው የምግብ ዘይት ለማቅረብ አንቅፋት እንደሆነባቸው ተናግረዋል። የማምረቻ ቦታ ችግር ያለባቸው መሆኑንም አቶ አዲስ ገልፀዋል። አዲሱ ማህበር ከሚመለከተው የመንግስት አካል ጋር በመሆን ጥራት ያለው የዘይት ምርት ለሀብረተሰቡ ለማቅረብ ያስችላል የሚል ተስፋ አንዳላቸውም አባላቱ ተናገረዋል። በምግብ ዘይት ማምረት የተሰማሩ ከ100 በላይ አምራች ፋብሪካዎች አባላትን ይዞ የተመሰረተው ይህ ማህበር ለዘርፉ ማነቆ የሆኑትን ችግሮች በመፈታት በተጠናከረ መልኩ ቀጣይነት ያለው እድገት ለማሳየት ከአባላቶቹ ጋር አንደሚሰራ ተገልጿል። የስብሰባው ተሳታፊዎች በቀረበው የመተዳደሪያ ደንብ ሰነድ ላይ ከመከሩ በኋላ አፅድቀውታል። ከመተዳደሪያ ደንቡ ውስጥም የማህበሩ የመመስረቻ ጽሁፍ ተዘጋጅቶ ለኢንዱስትሪ ሚኒስቴር የሚቀርብ ሲሆን በሚቀጥለው ሳምንትም ማህበሩ በይፋ ይመሰረታል ተብሎ ይጠበቃል።