ምርጫ ቦርድ በክርክርና ግጭት አፈታት ዙሪያ ለፖለቲካ ፓርቲ አመራሮች ስልጠና እየሰጠ ነው - ኢዜአ አማርኛ
ምርጫ ቦርድ በክርክርና ግጭት አፈታት ዙሪያ ለፖለቲካ ፓርቲ አመራሮች ስልጠና እየሰጠ ነው
አዲስ አበባ ነሐሴ 21/2010 የኢትዮጵያ ብሔራዊ የምርጫ ቦርድ ለአገር ዓቀፍና ክልላዊ የፖለቲካ ፓርቲ አመራሮች በክርክርና ግጭት አፈታት ላይ ዙሪያ በአዳማ ከተማ ስልጠና እየሰጠ ነው። የቦርዱ የህዝብ ግነኙነት ዳይሬክተር አቶ ተስፋለም አባይ ለኢዜአ እንደገለፁት፤ስልጠናው በሁለት ዙር ለፓርቲዎቹ የሚሰጥ ሲሆን ግማሽ ያህሉ ከዛሬ ጀምሮ ለሁለት ቀን ይሰለጥናሉ። “ስልጠናው በዴሞክራሲያዊ ክርክርና በግጭት አፈታት ላይ አለም አቀፍ ልምድ ለማካፈል የተዘጋጀ ነው'' ብለዋል። የቦርዱ ሰብሳቢ አምባሳደር ሳሚያ ዘካሪያ ቦርዱ ለፖለቲካ ፓርቲዎች የተለያዩ የአቅም ግንባታ ስራዎችን ሲሰጥ መቆየቱና ለወደፊትም በላቀ ደረጃ የፖለቲካ ፓርቲዎችን አቅም ለመገንባት ጠንክሮ እየሰራ መሆኑን ገልፀዋል። የፖለቲካ ፓርቲዎች ለመድብለ ፓርቲ ስርዓት ግንባታ ያላቸው አስተዋፅኦ ከፍተኛ በመሆኑ የፓርቲ አመራሮች የሚጠበቅባቸውን ኃላፊነት በሚገባ ለመወጣት የሚያከናውኑት ተግባር እንደተጠበቀ ሆኖ ቦርዱ የአቅም ግንባታ ስልጠናዎችን ጨምሮ የምክክር መድረኮችን በማዘጋጀት ለመድብለ ፓርቲ ስርዓት ግንባታ የበኩሉን እንደሚወጣ ተናግረዋል። የትኩረት አቅጣጫዎችን በመቅረፅ ቀጣይ የሚካሄዱ ምርጫዎች የበለጠ ዴሞክራሲያዊ፣ ነፃ እና በህዝብ ዘንድ ተዓማኒ ለማድረግ እንደሚሰራ ሰብሳቢዋ አሳውቀዋል። ስልጠናውን ምርጫ ቦርድ የኔዘርላንድ መልቲ-ፓርቲ ዴሞክራሲ ጋር በመተባበር ነው እየተሰጠ ያለው። አሁን ላይ በምርጫ ቦርድ የተመዘገቡት 40 ክልላዊና 22 አገር አቀፍ ፓርቲዎች ናቸው። በቅርቡ በተደረገው ጥሪ ወደ አገር ከመጡ የፖለቲካ ፓርቲዎች መካከል ለመመዝገብ ሂደት የጀመረ እንደሌለና በስልጠናውም እንዳልተሳተፉ አቶ ተስፋለም ተናግረዋል።