ቀጥታ፡

የዳያስፖራው አማራጭ የልማት አቅም

ለዓለም አቀፍ ፍልሰት መነሻ የሆኑ በርካታ ምክንያቶች እንዳሉ የተባበሩት መንግሥታት የስደተኞች ድርጅት በየዓመቱ የሚያወጣው ሪፖርት ያሳያል። መነሻው ምንም ይሁን ምን የውስጥና የውጭ 'ገፊ' እና 'ሳቢ' (push and pull factors) ሰበቦች ፍልሰትን እያባባሱት መሆኑን ጥናቶች ያረጋግጣሉ።

የኢትዮጵያዊያን የስደት ሁኔታም በጥናቱ በተጠቀሰው መሰረት በውስጣዊና ውጫዊ ሰበቦች መሆኑ አይቀርም። አንድም በአገር ውስጥ የፖለቲካ ሁኔታ ተማረው፣ የኢኮኖሚ አቅማቸውን ለማሻሻል ፈልገው፤ አንድም የትምህርት እድል አግኝተው ለስደት መዳረጋቸው የአደባባይ ምስጢር ነው። በአሁኑ ወቅት በሚሊዮን የሚቆጠሩ ኢትዮጵያዊያን በፖለቲካዊ አሊያም በኢኮኖሚያዊ ምክንያቶች ፈቅደው ይሁን ሳይፈቅዱ በተለያዩ አገራት ይኖራሉ።

አሁን ላይ ከሦስት ሚሊዮን የሚበልጡ ኢትዮጵያውያን በሁሉም የዓለማችን አህጉሮች (አንታርክቲካን ሳይጨምር) በስፋት እንደሚኖሩ ይታወቃል። የሚበዙት ደግሞ በሰሜን አሜሪካ፣ አውሮፓና መካከለኛ ምሥራቅ አገራት የሚኖሩ ናቸው።

እነዚህ ኢትዮጵያዊያን የዳያስፖራ ማኅበረሰብ አባላት በጠቅላይ ሚኒስትር ዐብይ አሕመድ የቀረበላቸውን ጥሪ ተቀብለው ከሁሉም ማዕዘናት ለገና እና ለጥምቀት በዓል ወደ አገር ቤት ገብተዋል፤ በመግባት ላይም ናቸው፡፡

የጠቅላይ ሚኒስትሩን ‘የታላቁ ጉዞ ወደ ሀገር ቤት’ ጥሪን ተቀብለው አንድ ሚሊዮን ኢትዮጵያዊያን ዳያስፖራዎች እና የኢትዮጵያ ወዳጆች ወደ አገር ቤት እንዲሚገቡ ይጠበቃል። ይህ ለአገርም ለመንግሥትም መልካም አጋጣሚ ነው።

የዳያስፖራ ማኅበሰረብ አባላት የውጭ ጫና እና ጣልቃ ገብነትን በመቃወም ከ30 በሚበልጡ የዓለም ከተሞች ያደረጉት ተቃውሞና ለኢትዮጵያ መንግሥት ያሳዩት አጋርነት በታሪክ የተለየ ስፍራ የሚሰጠው ነው። ኢትዮጵያም ለዳያስፖራ ማኅበረሰብ ጉዳዮች ልዩ ትኩረት የምትሰጥ አገር መሆኗ ደግሞ ተገቢነት እንዳለው የሚያሳይ ነው።

ይህን መልዕካም አጋጣሚ በመጠቀም ከፍተኛ ቁጥር ያላቸው የዳያስፖራ ማኅበረሰብ አባላትን በአገር ልማት ላይ ተሳትፏቸውን በማሳደግ አሻራቸውን እንዲያሳርፉ ማድረግ ይገባል።   

በእርግጥ መንግሥት የዳያስፖራ ኤጀንሲ በማቋቋም የዳያስፖራው ማኅበረሰብ አገራዊና ዓለም አቀፋዊ ሁኔታዎችን እንዲገነዘቡ ለማስቻል እየሰራ መሆኑ ምስጋና የሚቸረው ነው። ከዚህ ባለፈ ግን የዳያስፖራውን የኢኮኖሚ፣ የፖለቲካ፣ የቴክኖሎጂ፣ የዕውቀት፣ የክህሎት፣ ወዘተ…  ልምድና አቅምን በተቀናጀ መልኩ ለአገር ልማት ማዋል ያስፈልጋል። በዚህ ረገድ የሌሎች አገራት ተሞክሮ ወስዶ በአገራዊ ቅኝት ገርቶ ገቢራዊ ማድረግ ጠቃሚ ነው። 

ከቅርብ ዓመታት ወዲህ 'የዲያስፖራ አማራጭ' ከፍተኛየዳያስፖራ ማኅበረሰብ ባላቸው አገራት ቁልፍ የልማት ስትራቴጂ አካል እየሆነ መጥቷል። የእስያ እና የምስራቅ አውሮፓ እንዲሁም የላቲን አሜሪካ እና ካሪቢያን አገራት ለዲያስፖራ አማራጭ የተለየ ትኩረት በመስጠት የልማታቸው አጋር ለማድረግ ሰፊ ሥራ እየሰሩ ይገኛሉ።

የዲያስፖራ አማራጭ የስደተኞችን ሰብዓዊ፣ ኢኮኖሚያዊ እና ማህበራዊ አቅምን (capital) ለመጠቀም ያለመ የአገራት የፖሊሲ አቅጣጫ ነው። ከዚህ ሻገር ሲልም የዳያስፖራው ማኅበረሰብ ከመነሻ አገራት ጋር በኢንቨስትመንት፣ በክህሎት እና በልማት ያላቸውን ቁርኝት ለማጠናከር ታሳቢ ያደረገ ነው። ከዚህ አኳያ ኢትዮጵያ የተጠናከረ ሥራ በመስራት የዳያስፖራው ማኅበረሰብ በአገራዊ ልማት ላይ ያለውን ተሳተፊነት ማጎልበት ይኖርበታል።

አሁን አገሪቷ ያለባትን የውጭ ምንዛሬ እጥረት በማይናቅ ደረጃ ለመቃለል የዳያስፖራው ማኅበረሰብ በሃዋላ የሚላከው ገንዘብ (Remittance) ከፍ ያለ አስተዋጽኦ እንደሚያበረክት ይታመናል። ምክንያቱም በሃዋላ የሚላክ ገንዘብ ከሰሃራ በታች ባሉ የአፍሪካ አገራት ትልቅ እና የተረጋጋ የፋይናንስ ምንጭ በመሆኑ ኢትዮጵያም ይህን ዕድል በሚገባ ልትጠቀምበት ይገባል።

በቅርቡ የዓለም ባንክ እና ዓለም አቀፉ የፍልሰትና ልማት የዕውቀት አጋርነት በእንግሊዝኛ ምህፃሩ (KNOMAD) የተሰኘው ድርጅት እየተገባደደ ባለው የፈረንጆቹ ዓመት በዓለም አገራት ከውጭ የሚላከው የሃዋላ ፍሰት መጠን ወደ 589 ቢሊዮን ዶላር ከፍ ማለቱን ይፋ አድርጓል።

ይህ ደግሞ ከአምናው የፍስት መጠን በ ሰባት ነጥብ ሦስት በመቶ ብልጫ እንዳለው የሚያሳይ ነው። ከውጭ ወደ ሀገር ውስጥ የሚላከው ገንዘብ አሁን ላይ ይፋዊ የልማት ድጋፍን በሦስት እጥፍ ማስከንዳት ችሏል። ይህ ደግሞ ቻይናን ሳያካትት ከቀጥታ የውጭ ኢንቨስትመንት (FDI) እና  ከባህር ማዶ ልማት ድጋፍ (ODA) ጋር ሲነፃጸር ከ 50 በመቶ በላይ ብልጫ ያለው መሆኑ ከፍ ብሎ የተገለጸው እውነታን የሚያረጋግጥ ነው።

እየተገባደደ ባለው የፈረንጆቹ 2021 አምስት አገራት ቀዳሚ የሃዋላ ገንዘብ (Remittance) ተቀባይ ሆነው የተለዩ ሲሆን፤ ህንድ 83 ነጥብ 1 ቢሊዮን የአሜሪካ ዶላር በማግኘት ቀዳሚ አገር ሆናለች። ቻይና፣ ሜክሲኮ፣ ፊሊፒንስ እና የግብጽ ደግሞ በቅደም ተከተል ቀጣዩን ደረጃ ይዘዋል።

ባለፈው ዓመት ከኢትዮጵያ ዳያስፖራ ማኅበረሰብ አባላት ሁለት ነጥብ ስድስት ቢሊዮን  ዶላር ወደ አገር ቤት መላኩን የብሔራዊ ባንክ መረጃ ያስረዳል። ባለፉት ሦስት ተከታታይ ዓመታት ዳያስፖራው ዘጠኝ ቢሊዮን ዶላር የሚጠጋ ገንዘብ በሕጋዊ መንገድ ወደ አገር ቤት መላክ ችሏል።

እንዲያም ሆኖ ኢትዮጵያ ካላት ከፍተኛ የዳያስፖራ ማኅበረሰብ ቁጥር አኳያ ሲታይ ይህ የገንዘብ መጠን ከሚጠበቀው ውስጥ 30 በመቶ ብቻ መሆኑ ነው የሚነገረው። ይህ ደግሞ በዚህ ዙሪያ አሁንም ተጨማሪ ሥራዎች መስራት እንደሚገባ ነው የሚጠቁመው።

እዚህ ላይ ማነቆ ከሚሆኑት አንዱ የጥቁር ገበያ ጉዳይ ነው።  በኢትዮጵያ የውጭ ምንዛሬ ገበያ በይፋዊ እና በጥቁር ገበያ መካከል የጎላ የዋጋ ልዩነት መስተዋሉ ተጠቃሽ ችግር ተደርጎ ይወሰዳል። በባንኮች እና ትይዩ ገበያ (ጥቁር ገበያ) መካከል ያለው የዋጋ ልዩነት እየሰፋ መምጣት ዜጎች ከባንኮች ይልቅ ወደ ጥቁር ገበያ እንዲያዘነብሉ እያደረጋቸው ነው። በዚህ ረገድ መንግሥት ከሚወስዳቸው የማሻሻያ እርምጃዎች ባለፈ ጥቁር ገበያን ለመቆጣጠር የሚያደርገውን ጥረት ማጠናከር ይኖርበታል።

ሌላው በመደበኛ ማለትም በባንኮች በሃዋላ ለሚላከው ገንዘብ የሚጠየቀው ክፍያ ከፍተኛ መሆን ተጠቃሽ ነው። በፈረንጆቹ 2021 የመጀመሪያ ሩብ ዓመት በባንኮች ለሚላከው የሃዋላ ገንዘብ በአማካይ ስድስት ነጥብ አራት በመቶ ሲሆን፤ ይህ ወጪ ከፍተኛ እንደሆነ የዓለም ባንክ ሪፖርት ያሳያል። በተለይ ክፍያው ከሰሃራ በታች ባሉ የአፍሪካ አገራት ስምስት በመቶ መሆኑ ደግሞ እንደ ባንክ ያሉ መደበኛ የገንዘብ አስተላላፊዎች ተመራጭ እያደረጋቸው አይደለም። ስለዚህ መንግሥት ከህጋዊ የገንዘብ አስተላላፊዎች ጋር በመምከር የክፍያ ወጭውን ለማስተካከል የሚረዳ የፖሊሲ ምላሽ ሊያቀርብ ይገባል።

በተጨማሪም የዳያስፖራው ማኅበረሰብ ዲጂታል የባንክ ቻናሎች እንዲጠቀም ሁኔታዎች ማመቻቸት ያስፈልጋል። ሂደቱ ዲያስፖራው በዋናነት ገንዘቡን በህጋዊ መንገድ በባንኮች እንዲልክ ከማድረጉ ሕገ-ወጥ የገንዘብ ዝውውርን ለመቆጣጠር የሚጠቅምና እንደ አሸባሪው ህወሓትና ኦነግ-ሸኔ ያሉ የሽብር ቡድኖች የገንዘብ ምንጫቸውን ለማድረቅ የሚረዳ ጭምር ነው።

የፋይናንስ ዘርፉን መሠረተ ልማትን በማጠናከር እና በንግድ አገልግሎቶች አጠቃላይ ስምምነትን (General Agreement on Trade in Services) መሰረት በማድረግ ዓለም አቀፍ ጉዞዎችን (International Labor Mobility) ለዜጎች በማመቻቸት ከሃዋላ የሚገኘው የገንዘብ መጠን ማሳደግ ሌላው ሊተኮርበት የሚገባው ጉዳይ ነው።

እንደ ሌሎች አገራት ሁሉ ኢትዮጵያም ኢንቨስትመንትን ጨምሮ የዳያስፖራውን ሁለንተናዊ ተሳትፎ ለማሳደግ ከፖሊሲ ቀረፃ ባለፈ ተጨባጭ ሥራ መስራት ይጠበቅባታል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም