ዳያስፖራው ለኢትዮጵያ ህልውና ያደረገው ተጋድሎ ባንዳና ጠላትን ያስደነገጠና የኢትዮጵያዊያንን አንድነት በተግባር ያሳየ ነው - ኢዜአ አማርኛ
ዳያስፖራው ለኢትዮጵያ ህልውና ያደረገው ተጋድሎ ባንዳና ጠላትን ያስደነገጠና የኢትዮጵያዊያንን አንድነት በተግባር ያሳየ ነው
አዲስ አበባ፤ ታህሳስ 25 ቀን 2014 (ኢዜአ) "ዳያስፖራው ለኢትዮጵያ ህልውና ያደረገው ተጋድሎ ባንዳና ጠላትን ያስደነገጠና የኢትዮጵያዊያንን አንድነት በተግባር ያሳየ ነው'' ሲሉ የአፋር ክልል ርእሰ መስተዳድር አወል አርባ ተናገሩ፡፡
ዳያስፖራው በአፋር ክልል በአሸባሪው ህወሃት ጉዳት የደረሰባቸውን ግለሰቦችና ተቋማት በመደገፍ ረገድ እያደረገ ላለው አስተዋጽኦም ምስጋና አቅርበዋል፡፡
በአፋር ክልል ርእሰ መዲና ሰመራ የዲያስፖራ ሲምፖዚዬም እየተካሄደ ሲሆን፤ በመድረኩም የክልሉ ርእሰ መስተዳድር አወል አርባና የሰላም ሚኒስትር አቶ ብናልፍ አንዱዓለምን ጨምሮ በርካታ እንግዶች ተሳትፈዋል፡፡
ርእሰ መስተዳደሩ በዚህን ወቅት ዳያስፖራው በኢትዮጵያ ህልውና ዘመቻ አኩሪ ታሪክ መስራቱን ተናግረዋል፡፡
በ "#በቃ" ንቅናቄ ብርቱ ተጋድሎ አድርጋችኋል፤ ጫና ለማድረግ የሚፈልጉ አካላትን ደግሞ አሳፍራችኋል" ሲሉም ነው የተናገሩት፡፡
ንቅናቄው ለባንዳና ጠላት ትልቅ ድንጋጤ የፈጠረና የኢትዮጵያዊያንን አንድነት በተግባር ያሳየ ሁነት መሆኑንም ርእሰ መስተዳድሩ አንስተዋል፡፡
አሸባሪው ህወሃት በአማራና አፋር ክልሎች ሚሊዮኖች እንዲፈናቀሉ፤ በርካቶች በጅምላ እንዲጨፈጨፉ፣ ሴቶች እንዲደፈሩ ማድረጉንና በዚህም ኢትዮጵያ ጠልነቱን በተግባር እንዳሳየ ተናግረዋል።
የአፋር ህዝብ በአፋር በኩል ኢትዮጵያን ማፍረስ እንደማይቻል በተግባር ማረጋግጡን አንስተው፤ ኢትዮጵያዊያን ለአገራቸው ህልውና ዳግም የአደዋ ተጋድሎ ማድረጋቸውን ተናግረዋል፡፡
አፋርን በተለይም "ሚሌን ይዤ መደራደሪያ አድርጋለሁ' ያለው አሸባሪ ቡድኑ፤ የጸጥታ መዋቅሩ ከአፋር ህዝብ ጋር ሆኖ የእግር እሳት ሆኖበት ተመልሷል ብለዋል።
ድሉ በአገር ውስጥና የውጭ ኢትዮጵያዊያን ርብርብ እንደሆነ ሁሉ አሁንም በአገር ግንባታ ሌላ ድል መቀናጀት ይጠይቀናል ብለዋል።
"ኢትዮጵያን በአፋር በኩል መቼም መንካት እንደማይቻል አረጋግጣለሁ" ያሉት ርእሰ መስተዳድሩ፤ ኢትዮጵያዊነት እንደ ጃኬት የሚወልቅና የሚለበስ እንዳልሆነ ዳያስፖራው በተግባር አሳይቷል ብለዋል።
ዳያስፖራው ከዚህ ቀደም ሲያደርግ ለነበረው ሁሉን አቀፍ ድጋፍ አመስግነው፣ በቀጣይም በመልሶ ግንባታው አሻራቸውን እንዲያሳርፉ ጠይቀዋል።
ለበርካታ ኢንቨስትመንት አማራጮች በታደለውና የቱሪስት መዳረሻዎች በተቸረው አፋር ክልል ኢንቨስት በማድረግ እንዲሳተፉና አገርና ወገን እንዲጠቅሙ ጥሪ አቅርበዋል።
የሰላም ሚኒስትር አቶ ብናልፍ አንዱዓለም በበኩላቸው ኢትዮጵያ የገጠማትን ፈተና እንደወርቅ ተፈትና እያለፈች ነው፤ በዚህም ትውልዱ ደማቅ ታሪክ እየፃፈ ይገኛል ብለዋል።
አሸባሪ ቡድኑ የፈጸመው ጭካኔ የተሞላበት ግፍና ያደረሰው ውድመት የባዕድ አገር ወራሪ እንኳ ይፈፅመዋል ተብሎ የማይገመት መሆኑን ጠቅሰው፤ በመሆኑም ያጋጠመንን ችግር ተጋግዘን ማለፍ አለብን ነው ያሉት፡፡
ዳያስፖራው ወደ አገር ቤት መምጣቱ ታሪካዊ አጋጣሚ ነው ያሉት ሚኒስትሩ፤ ከመምጣቸው በፊትም በየአገራቱ ከኢትዮጵያ ጎን በመቆም ታሪክ የማይረሳው ታላቅ ጀብድ መፈጸማቸውን ተናግረዋል።
"ወደ አገር ቤት መምጣችሁ ዜጎቻቸውን እንዲወጡ የሚወተውቱ ጠላቶችን ሀሰተኛ ፕሮፓጋንዳ ያጋለጠና ኢትዮጵያዊያንን ያኮራ ነው" ሲሉም ተናግረዋል፡፡
በአፋር ክልል በአካል መገኘታችሁ ለክልሉ መልሶ ግንባታ አሻራ ለማስቀመጥ የምትጀሞሩበት አጋጣሚ ነው ብለዋል።
የኢትዮጵያ ዳያስፖራ ኤጀንሲ ምክትል ዋና ዳይሬክተር ዶክተር መሐመድ እድሪስ የዳያስፖራው ማህበረሰብ ተሳትፎ ለአገረ መንግስት ግንባታ ስኬት ወሳኝ ሚና እንዳለው ገልጸዋል፡፡
በመሆኑም ዳያስፖራው በአገሩ ጉዳይ ላይ ቀጣይነት ባለው መልኩ ንቁ ተሳትፎ እንዲያደርግ ጠይቀዋል፡፡