ቀጥታ፡

ለተፈናቀሉ ወገኖች የተሰበሰበው 200 ሺህ ዶላር በ‘አይዞን ኢትዮጵያ” የክፍያ አማራጭ ገቢ ተደረገ

ታህሳስ 25 ቀን 2014 (ኢዜአ) በአሜሪካ ዋሽንግተን ዲሲ፣ ሜሪላንድና ቨርጂኒያ ግዛቶች ከሚኖሩ ዳያስፖራዎችና የኢትዮጵያ ወዳጆች ለተፈናቀሉ ወገኖች የተሰበሰበው 200 ሺህ ዶላር በ‘አይዞን ኢትዮጵያ” የኦንላይን ገንዘብ ክፍያ አማራጭ ገቢ መደረጉ ተገለጸ።

የተፈናቀሉ ዜጎች መልሰው እስኪቋቋሙ ድረስ የሚደረገውን ድጋፍ ተጠናክሮ እንደሚቀጥልም ተነግሯል።

ታህሳስ 17 ቀን 2014 ዓ.ም በዋሽንግተን ዲሲ፣ ሜሪላንድና ቨርጂኒያ ግዛቶች በጦርነቱ ምክንያት ለተጎዱና ለተፈናቀሉ ወገኖች የገቢ ማሰባሰቢያ መርሃ ግብር በዋሽንግተን ዲሲና ሜሪላንድ መካሄዱ ይታወሳል።

በመርሃ ግብሩ እስካሁን ድረስ ከማህበረሰቡ እንዲሁም ከእምነትና ንግድ ተቋማት 300 ሺህ ዶላር መሰብሰቡን ‘ሚስ ኢትዮጵያ ዩኤስኤ ፓጀንት’ የተሰኘው ተቋም ለኢዜአ በላከው መግለጫ አስታውቋል።

ከተሰበሰበው 200 ሺህ ዶላር በ’አይዞን ኢትዮጵያ’ የኦንላይን ገንዘብ የክፍያ አማራጭ መላኩንና የተቀረው 100 ሺህ ዶላር ደግሞ ሌሎች ከሚደረጉ ተመሳሳይ የገቢ ማሰባሰቢያ መርሃ ግብሮች ከሚገኘው የገንዘብ መዋጮ ጋር ተደምሮ እንደሚላክ አመልክቷል።

በዋሽንግተን ዲሲ፣ ሜሪላንድና ቨርጂኒያ ከሚኖሩ ዳያስፖራዎችና የኢትዮጵያ ወዳጆች የተፈናቀሉ ዜጎች ሙሉ ለሙሉ እስኪቋቋሙ ድረስ የሚያደርጉትን ድጋፍ አጠናክረው እንደሚቀጥሉም ገልጿል።

በዋሽንግተን ዲሲ፣ ሜሪላንድና ቨርጂኒያ ግዛቶች በጦርነቱ ምክንያት ለተጎዱና ለተፈናቀሉ ወገኖች የተካሄደውን የገቢ ማሰባሰቢያ መርሃ ግብር ያዘጋጁት በግዛቶቹ የሚኖሩ የኪነ ጥበብ ባለሙያዎች ጥምረት፣ ‘ሚስ ኢትዮጵያ ዩኤስኤ ፓጀንት’፣ ሰላምና አንድነት ለኢትዮጵያ የዲሲ ግብረ ሃይል፣ የኢትዮጵያ ኮምዩኒቲ በሜሪላንድና የተለያዩ የሃይማኖት ተቋማት በጋራ በመሆን ነው።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም