ቀጥታ፡

2022 ኢትዮጵያ ከችግሯና ቁስሏ አገግማ ምርታማ የምትሆንበት ዓመት እንዲሆን እመኛለሁ

ታህሳስ 25 ቀን 2014 (ኢዜአ) “2022 ኢትዮጵያ ከችግሯና ቁስሏ አገግማ ምርታማ የምትሆንበት ዓመት እንዲሆን እመኛለሁ” ስትል ትውልደ ኢትዮጵያዊቷ አሜሪካዊ ጋዜጠኛ ሄርሜላ አረጋዊ ገለጸች።

“የአንድ ሚሊዮን ዳያስፖራ የአገር ቤት ጉዞ ጥሪ” ተቀብላ በቅርቡ ወደ ኢትዮጵያ እንደምትመጣም ገልጻለች።

ዓለም አቀፍ የኢትዮጵያ የተባበረ የዳያስፖራ ጥምረት የጠቅላይ ሚኒስትር አቢይ አህመድ ‘የአንድ ሚሊዮን ዳያስፖራ የአገር ቤት የጉዞ ጥሪ’ እና የጥምረቱን ስራ አስመልክቶ ያዘጋጀው የበይነ መረብ ውይይት ትናንት ተካሄዷል።

በውይይቱ ላይ የተሳተፈችው ትውልደ ኢትዮጵያዊቷ አሜሪካዊ ጋዜጠኛ ሄርሜላ አረጋዊ እ.አ.አ 2021 በኢትዮጵያ መጥፎ ዜናዎች የሚሰሙትና ዜጎቿም ለፈተና የተዳረጉበት ዓመት ነበር ብላለች።

የእ.አ.አ 2022 አዲስ ዓመት ኢትዮጵያ ከችግሯና ቁስሏ አገግማ ምርታማ የምትሆንበት ዓመት እንዲሆን እንደምትመኝ ገልጻ፤ በቅርቡ ወደ ኢትዮጵያ እንደምትመጣም ተናግራለች።

“ከኢትዮጵያ በሰባት ዓመቴ ከወጣሁ ጊዜ አንስቶ በተለያየ ጊዜ ወደ አገሬ ለመመለስ ፍላጎት ቢኖረኝም አልተሳካም፤ አሁን ወደ ኢትዮጵያ የምመጣበት ትክክለኛው ወቅት ነው” ብላለች ጋዜጠኛ ሄርሜላ።

ወደ ኢትዮጵያ በመልካም ስሜትና ተነሳሽነት እንደምትመጣና ኢትዮጵያን የሚጠቅሙ ስራዎችን እንደምታከናውን አመልክታለች።

“አንድ ሻንጣ ለወገኔ” ዘመቻ በኢትዮጵያውያንና ትውልደ ኢትዮጵያውያን የጤና ቁሳቁሶችን ወደ አገራቸው ይዘው እንዲሄዱ በሚደረገው እንቅስቃሴ ውስጥ እየተሳተፍኩ እገኛለሁ ብላለች።

ጋዜጠኛ ሄርሜላ ከኢትዮጵያ ዳያስፖራ ማህበረሰብ አባላት ጋር ያላትን ትስስር በማጠናከር በኢትዮጵያ ጉዳዮች ላይ የምታከናውነውን ተግባር እንደምትቀጥል ጠቁማለች።

ትውልደ ኢትዮጵያዊቷ አሜሪካዊ ጋዜጠኛ ሄርሜላ አረጋዊ በ’በቃ’ ወይም ‘#NoMore’ ዘመቻን በማስተባበርና የኢትዮጵያን እውነት ለዓለምአቀፉ ማህበረሰብ የማስረዳት ተግባር እያከናወነች ትገኛለች።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም