የኢትዮጵያ አየር መንገድ ወደ ላሊባላ ከተማ በረራ ጀመረ

166

ታህሳስ 25 ቀን 2014 (ኢዜአ) የኢትዮጵያ አየር መንገድ ወደ ላሊበላ ዕለታዊ በረራውን ዛሬ ጀምሯል።

ወደ ከተማዋ በረራ የሚያደርገው የመጀመሪያ አውሮፕላን ዛሬ ከጠዋቱ 2 ሰአት ከ30 ላይ ከቦሌ ዓለም አቀፍ አየር ማረፊያ መነሳቱን ኢዜአ ከአየር መንገዱ ያገኘው መረጃ ያመለክታል።

ወደ ከተማዋ መጓዝ የሚፈልጉ መንገደኞች በአየር መንገዱ መተግበሪያ በመጠቀም ቀጠሮ ማስያዝ እንደሚችሉ አስታውቋል።

የኢትዮጵያ አየር መንገድ ላሊበላን ጨምሮ ከ20 በላይ የአገር ውስጥ መዳረሻዎች አሉት።በኮቪድ-19 እና አሸባሪው ህወሃት በከፈተው ጦርነት ምክንያት ከተጎዱ በቱሪዝም ዘርፍ ከሚተዳደሩ አካባቢዎች አንዱ የላሊበላ ከተማ ነው።

የቱሪዝም ሚኒስትር አምባሳደር ናሲሴ ጫሊ የገና በዓል ታህሳስ 29 ቀን 2014 በብሔራዊ ደረጃ የአገር ውስጥና የውጭ እንግዶች በተገኙበት በላሊባላ ከተማ እንደሚከበርና ለዚህም የተለያዩ ዝግጅቶች መደረጋቸውን በሰጡት መግለጫ ተናግረዋል።

በዓሉ በከተማዋ መከበሩ የቱሪዝም ዘርፉን ለማነቃቃት ወሳኝ ሚና እንደሚኖረውም አመልክተዋል።

የላሊበላ ውቅር አብያተ ክርስቲያናት የተባበሩት መንግስታት ድርጅት የትምህርት፣የሳይንስና የባህል ድርጅት (ዩኔስኮ) የሚዳሰስ ቅርስ ብሎ ከመዘገባቸው የኢትዮጵያ ቅርሶች አንዱ ነው።

የላሊበላ ውቅር አብያተ ክርስቲያናት በ13ኛው መቶ ክፍለ ዘመን ከአለት ተፈልፍው የተሰሩ ሲሆን፤የኢትዮጵያ ስልጣኔ ማሳያ ተደርገው ይቆጠራሉ።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም