ዳያስፖራው የግብርና ክፍለ ኢኮኖሚውን ጨምሮ በተለያዩ የኢንቨስትመንት መስኮች በመሰማራት የመልሶ ማቋቋም ሂደቱን እንዲያፋጥን ጥሪ ቀረበ

71

ታህሳስ 24 ቀን 2014 (ኢዜአ) መንግስት ዳያስፖራው የግብርናው ክፍለ ኢኮኖሚ ጨምሮ በተለያዩ የኢንቨስትመንት መስኮች በመሰማራት የመልሶ ማቋቋም ሂደቱን እንዲያፋጥን ጥሪ አቀረበ።

ዓለም አቀፍ የኢትዮጵያ የተባበረ የዳያስፖራ ጥምረት የጠቅላይ ሚኒስትር አቢይ አህመድ ‘የአንድ ሚሊዮን ዳያስፖራ የአገር ቤት የጉዞ ጥሪ’ እና የጥምረቱን ስራ አስመልክቶ ያዘጋጀው የበይነ መረብ ውይይት እየተካሄደ ነው።

የመስኖና ቆላማ አካባቢዎች ሚኒስትር ኢንጂነር አይሻ መሐመድ አሸባሪው ሕወሓት በአማራና አፋር ክልሎች ፈጽሞት በነበረው ወረራ በዜጎችና በንብረት ከፍተኛ ጉዳት ማድረሱን ገልጸዋል።

የሽብር ቡድኑ በአፋር ክልል ንጹሃን ዜጎችን በመጨፍጨፍ ልጆችን ወላጅ አልባ፣ ዜጎችን አካል ጉዳተኛ፣ ማድረግን ጨምሮ ሌሎች አሰቃቂ የሰብአዊ መብት ጥሰቶችን ፈጽሟል ብለዋል።

የተለያዩ መሰረተ ልማቶችን በማውደም ዜጎችን ለችግር በመዳረግ ለሰብአዊነት ቅንጣት ያህል ደንታ እንደሌለው ማሳየቱን አመልክተዋል።

“ኢትዮጵያዊነትን ከምንም በላይ የሚያስቀድመው የአፋር ሕዝብ ሕይወቱን በመገበር የመጣውን ጠላት አሳፍሮ በመመለስ ለአገሩ ደጀን ሆኗል” ብለዋል ኢንጅነር አይሻ።

ይሁንና አሁንም አሸባሪው የሕወሓት ቡድን በአፋር ክልል ሕዝብ ላይ የሚያደርሰውን ትንኮሳ አለማቆሙንና በቅርቡ በክልሉ አብአላ ወረዳ ላይ በከባድ መሳሪያዎች በፈጸመው ጥቃት የበርካታ ንጹሃን ህይወት ማለፉን አመልክተዋል።

በተፈጸመው ጥቃትም በአብአላ ወረዳ ከ20 እስከ 30 ሺህ የሚሆኑ ዜጎች መፈናቀላቸውን ጠቁመዋል።

የሽብር ቡድኑ ድርጊት ለረጅም ጊዜ በጉርብትና የኖረውን የአፋር፣ አማራና ትግራይ ሕዝብ ደም ለማቃባት አላማ ያደረገ መሆኑን ተናግረዋል።

ቡድኑ በአማራና አፋር ክልሎች በዜጎች ላይ ያደረሰው ጉዳትና በንብረት ላይ ያደረሰውን ውድመት መልሶ ለማቋቋም በመንግስት በኩል እንቅስቃሴዎች መጀመራቸውን ነው ኢንጂነር አይሻ የገለጹት።

ወደ ኢትዮጵያ እየመጣ ያለው ዳያስፖራ ለመልሶ ማቋቋም ሂደቱ ወሳኝ ሚና ይኖረዋል ብለዋል።

ዳያስፖራው የግብርና ክፍለ ኢኮኖሚውን ጨምሮ በሌሎች የኢንቨስትመንት መስኮች በመሰማራት የመልሶ ማቋቋሙን ስራ እንዲያፋጥን ኢንጂነር አይሻ ጠይቀዋል።

አፋር ክልል በማዕድን ፣ቱሪዝምና እንስሳ ሀብት እምቅ አቅም እንዳለውና ዳያስፖራው በነዚህ መስኮች ቢሰማራ ውጤታማ እንደሚሆን ገልጸዋል።

በተለይም ኢትዮጵያ በግብርና፣ በመስኖና በውሃ ሃብት ያላትን እምቅ አቅም በአግባቡ ከተጠቀመች አሁን ካለችበት ችግር ከመውጣት ባለፈ በዘላቂነት የምግብ ሉዓላዊነቷን ማረጋገጥ ትችላለች ብለዋል።

በዚህ ረገድ ዳያስፖራው በእውቀቱና በገንዘቡ ድጋፍ ማድረግ እንደሚኖርበት አመልክተዋል።

ኢትዮጵያ ያሏትን የተፈጥሮ ሀብቷን አሟጣ በመጠቀም ከተረጂነት እንድትላቀቅ ዳያስፖራውን ጨምሮ ሁሉም ዜጋ በተባበረ ክንድ መስራት እንዳለበት ገልጸዋል።

በጦርነቱ ምክንያት ለከፍተኛ የስነ ልቦና ቀውስ የተዳረጉ ዜጎችን ቁስል ማከም ልዩ ትኩረት ሊሰጠው እንደሚገባም ነው ኢንጂነር አይሻ ያስገነዘቡት።

ዳያስፖራው ኢትዮጵያ የሚደርስባትን ዓለም አቀፍ ጫና በመመከትና ለተጎዱ ወገኖች እያደረገ ላለው ድጋፍም ምስጋና አቅርበው ድጋፉ እንዲቀጥል ጥሪ አቅርበዋል።

ዓለም አቀፍ የኢትዮጵያ የተባበረ የዳያስፖራ ጥምረት ፕሬዚዳንት አቶ አለባቸው ደሳለኝ በበኩላቸው ዳያስፖራው አሁን ከሚያደርገው ድጋፍ ባለፈ በጥናትና እቅድ ላይ የተመሰረተ ዘላቂ ድጋፍ ለኢትዮጵያ ለማድረግ እየሰራ ነው ብለዋል።

በመልሶ ማቋቋምና ግንባታ፣ የውጭ ምንዛሬ እጥረትን መቅረፍ፣ በሀብት ማሰባሰብና በአጠቃላይ የኢትዮጵያ እድገትና ልማት የሚደግፉ ስራዎችን ለማከናወን ዝግጁ መሆኑን አመልክተዋል።

ዳያስፖራው በአስቸጋሪ ወቅት ላይ የምትገኘውን ኢትዮጵያ ካለችበት ፈተና ለማውጣት ባለው አቅም ሁሉ ድጋፍ እንደሚያደርግ አመልክተዋል።

ዓለም አቀፍ የኢትዮጵያ የተባበረ የዳያስፖራ ጥምረት ባዘጋጀው የበይነ መርሃ ግብር የዳያስፖራ ማህበረሰብ አባላት፣ ታዋቂ ሰዎች፣ የኪነ ጥበብ ባለሙያዎች የመንግስት ከፍተኛ የስራ ሃላፊዎችና ሌሎች ጥሪ የተደረገላቸው እንግዶች ተገኝተዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም