ታሪካዊና ጥንታዊ ቅርሶች ለእይታ መቅረባቸው ኢትዮጵያ በቱሪዝም ዘርፉ ያላትን እምቅ አቅም ያሳያል - ኢዜአ አማርኛ
ታሪካዊና ጥንታዊ ቅርሶች ለእይታ መቅረባቸው ኢትዮጵያ በቱሪዝም ዘርፉ ያላትን እምቅ አቅም ያሳያል
ጎንደር ታህሳስ 24/2014 (ኢዜአ) ታሪካዊና ጥንታዊ ቅርሶች ለህዝብ እይታ መቅረባቸው ኢትዮጵያ በቱሪዝም ዘርፍ ያላትን እምቅ አቅም ያሳያል ሲሉ የኢትዮጵያ የቅርስ ጥናትና ጥበቃ ባለስልጣን ዋና ዳይሬክተር ረዳት ፕሮፌሰር አበባው አያሌው አስታወቁ።
የአጼ ቴዎድሮስ ቁንዳላ ሹሩባን ጨምሮ ታሪካዊና ጥንታዊ ቅርሶች ዛሬ ጎንደር ከተማ ሲገቡ በከፍተኛ የክብር ስነ ስርአት አቀባባል ተደርጎላቸዋል፡፡
የባለስልጣኑ ዋና ዳይሬክተር ረዳት ፕሮፌሰር አበባው አያሌው እንደገለጹት የአጼ ቴዎድሮስ ቅርሶች መላው የኢትዮጵያ ህዝብ ለውጭና ለውስጥ ጠላቶች አንበረከክም ባልንበት ወቅት ለህዝብ እይታ መቅረቡ ታሪካዊነቱን ያጎላዋል።
ታሪካዊና ጥንታዊ ቅርሶች ለህዝብ እይታ መቅረባቸው ኢትዮጵያ በቱሪዝም ዘርፍ ያላትን እምቅ አቅም አጉልቶ በማሳየት የቱሪስት ፍሰቱን ለማጠናከር አቅም የሚፈጥር መሆኑን አመልክተዋል።
የአጼ ቴዎድሮስን ቅርሶችን ጨምሮ ከ20 በላይ ከመቅደላ ተዘርፈው የነበሩ ቅርሶች በጎንደር ከተማ በሚገኘው የራስ ግምብ ሙዚየም በክብር ለጎብኚዎች ክፍት እንደሚደረጉ ተናግረዋል፡፡
"የአጼ ቴዎድሮስ ታሪካዊና ጥንታዊ ቅርሶች ወደ ጎንደር መምጣት ጥምቀትን በታላቅ ድምቀት ለምታከብረው ጎንደር ልዩ የበአል ድባብ የሚፈጥር ነው" ያሉት ደግሞ የከተማው ተቀዳሚ ምክትል ከንቲባ አቶ ዘውዱ ማለደ ናቸው፡፡
"አጼ ቴዎድሮስ የአንድነት የጀግንነት የጽናትና የዘመናዊ ስልጣኔ አስተሳሳብ በር ከፋች ታሪካዊ መሪ ናቸው "ሲሉ ተናግረዋል፡፡
ከነገ ሰኞ ጀምሮ ለህዝብ እይታ ክፍት የሚሆኑት የአጼ ቴዎድሮስ ታሪካዊና ጥንታዊ ቅርሶችን ህዝቡ እንዲጎበኝ ጥሪ አቅርበዋል፡፡
በከተማው ፒያሳ አደባባይ በሚገኘው የአጼ ቴዎድሮስ መታሰቢያ ሃውልት ላይ በተካሄደው የአቀባበል ስነ-ሰርአት ላይ የፌደራል፣ የክልልና የከተማ አስተዳዳሩ አመራሮች፣ አርቲስቶች ፣ጀግኖች አርበኞች የሃይማኖት አባቶችና የከተማው ነዋሪዎች ተገኝተዋል፡፡