ቀጥታ፡

‘ስለ ኢትዮጵያ’ በሚል ርዕስ የተዘጋጀ የፎቶግራፍ አውደ ርዕይ ከነገ ጀምሮ ይካሄዳል

ታህሳስ 24 ቀን 2014 (ኢዜአ) የኢትዮጵያ ፕሬስ ድርጅት ‘ስለ ኢትዮጵያ’ በሚል ርዕስ ያዘጋጀው የፎቶፍራፍ አውደ ርዕይ ከነገ ጀምሮ በድርጅቱ ዋና መስሪያ ቤት ይካሄዳል።

አውደ ርዕዩ ኢትዮጵያና ሕዝቦቿ አገርን ለማዳን ያደረጉትን ተጋድሎ ያሳያል።

የኢትዮጵያ ፕሬስ ድርጅት ዋና ስራ አስፈጻሚ አቶ ጌትነት ታደሰ አውደ ርዕዩ ድርጅቱ ላለፈው አንድ ዓመት ከሁለት ወር በዘለቀው ጦርነት በፎቶ የሰነዳቸውን ኩነቶች የሚታዩበት እንደሆነ ለኢዜአ ገልጸዋል።

በትግራይ ክልል የአገር መከላከያ ሰራዊት ሰሜን ዕዝ ከሕዝቡ ጋር የነበረው መስተጋብርና ያበረከተው አስተዋጽኦ፣ የደረሰበት ጥቃትና ጉዳት እንዲሁም አገርን ለማዳን የከፈለውን መስዋዕትነት የሚሳዩ ፎቶዎች በአውደ ርዕዩ ላይ እንደሚታዩ ተናግረዋል።

የኢትዮጵያ ሕዝብ ለአገር መከላከያ ሰራዊት ያደረገው ድጋፍ እንዲሁም አሸባሪው የሕወሓት ቡድን በአማራና አፋር ክልሎች ፈጽሞት በነበረው ወረራ በዜጎች ላይ ያደረሰውን አሰቃቂ ድርጊቶችና በተለያዩ ተቋማት ላይ ያደረሰውን ከፍተኛ ውድመትና ዝርፊያ የሚያሳዩ ፎቶዎች ለሕዝብ እይታ ይቀርባሉ ብለዋል።

አውደ ርዕዩ ‘ኢትዮጵያ አሸንፋ ትሻገራለች’ የሚለውን እሳቤ የያዘ እንደሆነና በዚህ ረገድም “ኢትዮጵያና ሕዝቦቿ ኢትዮጵያን ለማዳንና የጠላትን አገር የማፍረስ እኩይ አላማ ለማክሸፍ ያደረጉትን ተጋድሎ” የሚሳይ መሆኑን ነው አቶ ጌትነት የገለጹት።

ኢትዮጵያውያን ባለፈው አንድ ዓመት ከሁለት ወር ውስጥ የነበረውን ሁኔታ ዳግም መለስ ብለው እንዲያዩት ከማድረግ አኳያ አውድ ርዕዩ ወሳኝ ሚና እንደሚኖረው አመልክተዋል።

የጠቅላይ ሚኒስትር አቢይ አህመድ “የአንድ ሚሊዮን ዳያስፖራ የአገር ቤት ጉዞ ጥሪን ተከትሎ” በርከት ባለ ሁኔታ ወደ ኢትዮጵያ እየመጡ ያሉ ኢትዮጵያውያንና የኢትዮጵያ ወዳጆች የነበረውን ሁኔታ በደንብ እንዲረዱ እድል የሚፈጥር መሆኑን ገልጸዋል።

ከታህሳስ 25 እስከ ጥር 12 ቀን 2014 ዓ.ም የሚቆየውን አውድ ርዕይ ኢትዮጵያውያን፣ የዳያስፖራ ማህበረሰብ አባላት፣ የውጪ አገር ዜጎች፣ ዲፕሎማቶችና ሌሎች የሕብረተሰብ ክፍሎች ይጎበኙታል ተብሎ ይጠበቃል።

ነገ በሚከፈተው አውደ ርዕይ መክፈቻ ስነ ስርዓት ላይ የመንግስት ከፍተኛ የስራ ሃላፊዎች፣ የመገናኛ ብዙሃን ሃላፊዎችና ሌሎች ጥሪ የተደረገላቸው እንግዶች ይገኛሉ ተብሏል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም