የደቡብ ክልል ሕዝብ በህልውና ዘመቻው ያሳየውን ህብረት በድህረ ጦርነት ወቅት መድገም ይጠበቅበታል - ኢዜአ አማርኛ
የደቡብ ክልል ሕዝብ በህልውና ዘመቻው ያሳየውን ህብረት በድህረ ጦርነት ወቅት መድገም ይጠበቅበታል
ሀዋሳ ፤ታህሳስ 24/2014(ኢዜአ)የደቡብ ክልል ሕዝብ በህልውና ዘመቻው ያሳየውን አንድነትና ህብረት በድህረ ጦርነት ወቅት መድገም እንደሚጠበቅበት ተመለከተ።
የብልፅግና ፓርቲ የደቡብ ክልል ጽህፈት ቤት የክልል፣ ዞኖችና ልዩ ወረዳዎች ከፍተኛ አመራሮች በወቅታዊ ክልላዊና ሀገራዊ ጉዳይ ላይ ሲያካሄዱ የቆዩት የምክክር መድረክ መጠናቀቁን አስመልክቶ መግለጫ ተሰጥቷል።
በጽህፈት ቤቱ የህዝብ ግንኙነትና ሚዲያ ዘርፍ ኃላፊ አቶ ኸይረዲን ረዲ በሰጡት መግለጫ፤የሀገሪቱ የትኩረት አቅጣጫ በመደመርና በአብሮነት ላይ የተመሰረተ ቢሆንም፤ ለሠላም ዋጋ በማይሰጠው አሸባሪው ህወሓት ተገዳ ወደ ጦርነት መግባቷን ተናግረዋል፡፡
''የጦርነቱ የመጀመሪያው ምዕራፍ በኢትዮጵያዊያን አሸናፊነት ተደምድሟል'' ያሉት አቶ ኸይረዲን፣ በሁሉም የሀገሪቱ ጫፍ ያሉት ኢትዮጵያዊያን በግንባር ፣ በደጀንነትና የሞራል ድጋፍ ማድረጋቸውን አስታውሰዋል ፡፡
በህልውና ዘመቻው የተገኘውን የሕዝብ አንድነትና መተባበርን አጠናክሮ በማስቀጠልና ኃይልን በማሰባሰብ በድህረ ጦርነት የሚገጥሙ ፈተናዎችን መቋቋም እንደሚያስፈልግ ገልጸው፤ በምክክር መድረኩም አመራሩ አፅንኦት ሰጥቶ እንደተወያየበት ጠቁመዋል፡፡
የክልሉን ሕዝብ የመልካም አስተዳደርና የልማት ጥያቄዎችን መመለስ ትኩረት እንደተሰጠው ያነሱት ኃላፊው፤ በተለይ በክልሉ በይደር የቆዩ በክልል የመደራጀት ጥያቄዎች የሕዝብን አብሮነት እንዲሁም የጋራ ተጠቃሚነትን በሚያስቀጥል መልኩ ምላሽ እንዲያገኙ አቅጣጫ እንደተቀመጠም አመልክተዋል፡፡
የሕዝብ አንድነት ማጠናከርና የክልሉን ሠላምና ደህንነት ማስጠበቅ ሌላው የመወያያ አጀንዳ እንደነበር አቶ ኸይረዲን አውስተዋል፡፡
በጦርነቱ ሳቢያ ሊከሰት የሚችለውን የኢኮኖሚ ችግር ለመቋቋምም በክልሉ ያሉ የሰው ኃይል ፣ የመሬትና የውሀ ሀብቶችን አሟጦ በመጠቀም ምርትና ምርታማነትን ማሳደግ እንዲሁም የቁጠባ ባህልን ለማሳደግ ትኩረት እንዲሰጥ ተጠይቋል ነው ያሉት ፡፡
ሕዝቡ በህልውና ዘመቻው ያሳየውን ህብረት በድህረ ጦርነት ወቅት መድገም እንደሚጠበቅበት ተመልክቷል።
በዚህም በአማራና አፋር ክልል አሸባሪው በከፈተው ጦርነት የተፈናቀሉ ወገኖችን መልሶ ለማቋቋምና የፈረሱ መሠረተ ልማት ተቋማትን መገንባት እንደሚያስፈልግ መወሳቱን ጠቅሰዋል።
እንዲሁም የሕዝብ ለሕዝብ ግንኙነትን ወደ ላቀ ደረጃ ማድረስ በመድረኩ አፅንኦት እንደተሰጠውም ገልጸዋል፡፡
የድህረ ጦርነት የትኩረት አቅጣጫዎችን ለማሳካት አመራሩ ከሕዝብ ጋር በመቀራረብ መስራት እንዳለበትና ለዚህም የአመለካከትና የተግባር አንድነት የሚፈጥር መግባባት ላይ መደረሱን አስረድተዋል።