ቀጥታ፡

የአጼ ቴዎድሮስ ቁንዳላና ሌሎች ጥንታዊና ታሪካዊ ቅርሶች ጎንደር ገቡ

ጎንደር ታህሳስ 24/2014 (ኢዜአ ) የአጼ ቴዎድሮስ ቁንዳላ(ሹሩባ)ና ሌሎች ጥንታዊና ታሪካዊ ቅርሶች ጎንደር ከተማ ገቡ ።


ቅርሶቹ ዛሬ ጎንደር ከተማ ሲደርሱ በከተማው አስተዳደር አካላትና በነዋሪው ህብረተሰብ ደማቅ የአቀባበል ስነ ስርአት ተካሂዷል።

የጎንደር ከተማ አስተዳደር ባህልና ቱሪዝም መምሪያ ሃላፊ አቶ ቻላቸው ዳኘው ለኢዜአ እንደገለጹት ወደ ጎንደር የገቡት ቅርሶች በመቅደላ ጦርነት ተዘርፈው ወደ እንግሊዝ አገር ከተወሰዱ ከ150 ዓመት በኋላ የተመለሱ ናቸው።

ለቅርሶቹ በከተማው ፒያሳ አደባባይ በሚገኘው የአጼ ቴዎድሮስ መታሰቢያ ሃውልት ደማቅ የአቀባበል ስነ ስርዓት መካሄዱን ተናግረዋል።

ዛሬ ጎንደር የገቡት ቅርሶች የአጼ ቴዎድሮስ ቁንዳላ(ሹሩባ)፣ጋሻና ጎራዴ፣ የጸሎት መጻህፍትና ሌሎች 13 የሚሆኑ ታሪካዊና ጥንታዊ ቅርሶች መሆናቸውን ተናግረዋል።

ቅርሶቹ ከነገ ጀምሮ በራስ ግንብ ሙዚየም ለህዝብ እይታ እንደሚቀርቡ አመላክተዋል።

ቅርሶቹ ጎንደር የገቡት በከተማው በየአመቱ በድምቀት የሚከበረውን የጥምቀት በዓል ለመታደም ከውጭና የአገር ውስጥ  ለሚመጡ ጎብኝዎች አማራጭ መስህብ በመፍጠር የቆይታ ጊዜያቸውን ለማራዘም ታስቦ መሆኑን አብራርተዋል።

የጎንደር ከተማ ተቀዳሚ ምክትል ከንቲባ አቶ ዘውዱ ማለደን ጨምሮ የጎንደር ዩኒቨርሲቲ ፕሬዝዳንት፣ የፌደራል፣ የክልልና የከተማ አስተዳደሩ ከፍተኛ አመራሮችና ነዋሪው ህብረተሰብ በአቀባበል ስነ ስርዓቱ ላይ ታድመዋል።

የጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ አህመድ ጥሪን ተከትሎ በውጭ የሚኖሩ ኢትዮጵያዊያንና ትውልደ ኢትዮጵያዊያን ወደ ሀገር ቤት እየገቡ ሲሆን በየአካቢውም አቀባበል እየተደረገላቸው መሆኑ ይታወቃል።

በጎንደር በየአመቱ የሚከበረው የጥምቀት በአል ከፍተኛ ቁጥር ያላቸው የሀገር ውስጥና የውጭ ጎብኝዎች የሚታደሙበት ነው።

እንደ አውሮፓ አቆጣጠር  በ1868 መቅደላ ላይ አጼ-ቴዎድሮስ ‘ለእንግሊዝ ወታደሮች እጅ አልሰጥም’ ብለው ራሳቸውን እንደሰዉ የታሪክ ድርሳናት ይገልፃሉ።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም