ቀጥታ፡

አሸባሪው ህወሃት በመካነ ኢየሱስ ማዕከላዊ ሰሜን ኢትዮጵያ ሲኖዶስ ላይ 23 ሚሊዮን ብር ግምት ያለው ውድመት አድርሷል

ታህሳስ 24/2014/ኢዜአ/ አሸባሪው የህወሃት ቡድን በኢትዮጵያ ወንጌላዊት ቤተ-ክርስቲያን መካነ ኢየሱስ ማዕከላዊ ሰሜን ኢትዮጵያ ሲኖዶስ ላይ 23 ሚሊዮን ብር ግምት ያለው ውድመት ማድረሱን የማዕከላዊ ሰሜን ኢትዮጵያ ሲኖዶስ አስታወቀ፡፡

አሸባሪው የህወሃት ቡድን በአማራና አፋር ክልሎች በወረራ ይዟቸው በቆየባቸው አካባቢዎች የሃይማኖት ተቋማትን ጨምሮ የትምህርት፣ የጤና እና ሌሎች የህዝብ መገልገያ ተቋማት ላይ ውድመትና ዘረፋ መፈጸሙ ይታወቃል፡፡

ቡድኑ ውድመትና ዘረፋ ከፈጸመባቸው የእምነት ተቋማት መካከል በደሴ ከተማ የሚገኘው የኢትዮጵያ ወንጌላዊት ቤተ-ክርስቲያን መካነ ኢየሱስ ማዕከላዊ ሰሜን ኢትዮጵያ ሲኖዶስ አንዱ ነው፡፡

የሶኖዶሱ ፕሬዚዳንት ቄስ ዋኘው አንዳርጌ ከኢዜአ ጋር በነበራቸው ቆይታ አሸባሪ ቡድኑ በሲኖዶሱ ቅጥር ጊቢ አገልግሎት ሲሰጡ የነበሩ ሶስት ተሽከርካሪዎችንና ስምንት ሞተር ሳይክሎችን መዝረፉን ተናግረዋል፡፡

የሽብር ቡድኑ ታጣቂዎች ሌሎች በርካታ ንብረቶችን መዝረፋቸውንና መውሰድ ያልቻሉትን ደግሞ ማውደማቸውንም እንዲሁ፡፡

እንደ ቄስ ዋኘው ገለጻ፤ ቤተ-ክርስቲያኗ በሰሜን ኢትዮጵያ በርካታ የልማት ስራዎችን በመስራት ህዝቡን ተጠቃሚ ስታደርግ ቆይታለች፡፡

በተለይ በትግራይ ክልል ትምህርት ቤቶችን በመክፈት፣ ሆስፒታሎችን በመገንባት እና ህብረተሰቡ ንጹህ የመጠጥ ውሃን እንዲያገኝ ከማድረግ አንጻር በርካታ ስራዎችን ማከናወኗን ገልጸዋል፡፡

"በመሆኑም ቤተክርስቲያኗ ላይ ይህ አይነቱ አሳፋሪ ድርጊት ሊፈጸም አይገባም ነበር" ሲሉም ነው የተናገሩት፡፡

የሽብር ቡድኑ ታጣቂዎች እርሳቸውን ጨምሮ በሲኖዶሱ ቅጥር ግቢ ያገኟቸውን የእምነት አባቶች በመሳሪያ በማስፈራራትና በማሰቃየት ዝርፊያ መፈጸማቸውን የተናገሩት ደግሞ ሌላኛው ቤተ-ክርስቲያኗ የሃይማኖት አባት ቄስ ሞላ አሰፋ ናቸው፡፡

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም