በእስራኤል የሚኖሩ የኢትዮጵያ ማህበረሰብ አባላት በመልሶ ግንባታና ማቋቋም ሂደት ተሳትፎ ማድረግ የሚያስችል ስራ ጀምረዋል - ኢዜአ አማርኛ
በእስራኤል የሚኖሩ የኢትዮጵያ ማህበረሰብ አባላት በመልሶ ግንባታና ማቋቋም ሂደት ተሳትፎ ማድረግ የሚያስችል ስራ ጀምረዋል
ታህሳስ 24/2014/ኢዜአ/ በእስራኤል የሚኖሩ የኢትዮጵያ ማህበረሰብ አባላት በመልሶ ግንባታና ማቋቋም ሂደት ተሳትፎ ማድረግ የሚያስችል ስራ መጀመራቸውን የቀድሞ የእስራኤል ፓርላማ(ክኔሴት) አባል ሽሎሞ ሞላ ገለጹ።
አሸባሪው ሕወሓት በአማራና አፋር ክልል ወረራ በፈጸመበት ወቅት በሰው ሕይወትና ንብረት ላይ ከባድ ጉዳት ማድረሱ ይታወቃል።
የሽብር ቡድኑ በሁለቱ ክልሎች ከፍተኛ የሆነ የንብረት ውድመት አድርሷል፤የተደራጀ ዝርፊያም ፈጽሟል።
ዳያስፖራው በዜጎች ላይ የደረሰውን ሰብአዊ ቀውስና የወደሙ ንብረቶችን መልሶ ለማቋቋምና መልሶ ለመገንባት እየተደረገ ያለውን ጥረት እንዲደግፍ መንግስት ጥሪ ማድረጉ ይታወቃል።
የቀድሞው የእስራኤል ፓርላማ(ክኔሴት) አባል ሽሎሞ ሞላ በእስራኤል የኢትዮጵያ ኮምዩኒቲ አባላት መንግስት ለመልሶ ማቋቋም ያቀረበውን ጥሪ በመቀበል ድጋፍ ለማድረግ እንቅስቃሴ መጀመራቸውን ለኢዜአ ገልጸዋል።
በእስራኤል የሚገኙ ዳያስፖራዎች በተለይም የንግድ ማህበረብ አባላት ውድመት በደረሰባቸው አካባቢዎች መዋዕለ ነዋያቸውን በማፍሰስ ኢኮኖሚውን እንዲያነቃቁ ቅስቀሳ እየተደረገ ስለመሆኑ ጠቅሰው፤ በዚህም የታየውም ፍላጎት አበረታች የሚባል እንደሆነ ተናግረዋል።
ሐኪሞች፣መሐንዲሶችና በተለያዩ መስኮች የተሰማሩ ባለሙያዎች በእውቀታቸውና በክህሎታቸውኢትዮጵያን ማገዝ ይፈልጋሉ፤መንግስትም ባለሙያዎቹ አገራቸውን የሚያገለግሉበት አሰራር ሊዘረጋ ይገባል ብለዋል።
"ኢትዮጵያ በዘላቂነት የኢኮኖሚ እድገቷን ማረጋገጥ የምትችልበት የውሃ፣መሬትና ሌሎች የተፈጥሮ ሀብቶች አሏት" ያሉት ሽሎሞ፤ ይህን አቅም ለመጠቀም የሚያስችል ቴክኖሎጂዎች አስፈላጊ መሆናቸውን አመልክተዋል።
ከዚህ አኳያ በእስራኤል የሚገኙ ዳያስፖራዎች ኢትዮጵያ በቴክኖሊጂ በመታገዝ የተፈጥሮ ሃብቷን መጠቀም እንድትችል የሚያግዙ ፕሮጀክቶችን መንደፋቸውን አስረድተዋል።
በተለይ የእርሻ ቴክኖሎጂ ድጋፍ ለኢትዮጵያ የግብርና ዘርፍ እድገት ወሳኝ ሚና እንደሚኖረውና በዚህ ረገድ የእስራኤል ተሞክሮን እንደ ማሳያ እንደሚወሰድ አብራርተዋል።
በእስራኤል የሚኖሩ የኢትዮጵያ ማህበረሰብ አባላት በሕጋዊ መንገድ ብቻ ወደ አገር ቤት ገንዘብ በመላክ የኢትዮጵያን ኢኮኖሚ እንዲደግፉ ግንዛቤ የመፍጠር ስራ እየተከናወነ እንደሚገኝም ጨምረው ገልጸዋል።
የዳያስፖራው ማህበረሰብ በአሸባሪው ህወሃት ወረራ ለተፈናቀሉ ዜጎች በገንዘብና በአይነትድጋፍ እያደረገ እንደሚገኝ ጠቅሰው፤ ይህ ተግባርም ተጠናክሮ ይቀጥላል ነው ያሉት።
ዳያስፖራው በመንግስት የቀረበውን ጥሪ ተቀብሎ በመልሶ ግንባታና ማቋቋሙ ሂደት የነቃ ተሳትፎ እንዲያደርግም ጥሪ አቅርበዋል።
ዳያስፖራው በሕጋዊ መንገድ ገንዘብ ወደ አገር ቤት በመላክ እንዲሁም በንግድና ኢንቨትመንት ላይ በንቃት በመሳተፍ የኢትዮጵያን ኢኮኖሚ በዘላቂነት መደገፍ አለበት ብለዋል።
ዳያስፖራው በ’አይዞን ኢትዮጵያ’ የገንዘብ ማሰባሰቢያ አማራጭ እና በውጭ አገራት በሚገኙ ሚሲዮኖች አማካኝነት ለተፈናቀሉ ዜጎች ከ400 ሚሊዮን ብር በላይ ድጋፍ ማድረጉን ኢዜአ ከኢትዮጵያ ዳያስፖራ ኤጀንሲ ያገኘው መረጃ ያመለክታል።
ሁለት ወር ባልሞላ ጊዜ ውስጥ በ’አይዞን ኢትዮጵያ’ አማካኝነት ለተፈናቀሉ ወገኖች የሚውል ከ256 ነጥብ 9 ሚሊዮን ብር በላይ ገንዘብ ከዳያስፖራው መሰብሰቡም ተገልጿል።
በ2014 ዓ.ም የበጀት ዓመት አምስት ወራት በኢንቨስትመንትና ንግድ ላይ ለመሰማራት የ22 ነጥብ 4 ቢሊዮን ብር ካፒታል ያስመዘገቡ 339 ዳያስፖራዎች ፍላጎት ማሳየታቸውን ኤጀንሲው አመልክቷል።