ድርጅቱ በአፋር በጦርነት ለተጎዱ ወገኖች ከ40 ሚሊዮን ብር በላይ የሚገመት የምግብ ድጋፍ አደረገ - ኢዜአ አማርኛ
ድርጅቱ በአፋር በጦርነት ለተጎዱ ወገኖች ከ40 ሚሊዮን ብር በላይ የሚገመት የምግብ ድጋፍ አደረገ
ሰመራ፤ ታህሳስ 23 ቀን 2014 (ኢዜአ) የሠዎች ለሰዎች በጎ-አድራጎት ድርጅት በአፋር ህወሀት በከፈተው ጦርነት ለተጎዱ ወገኖች ከ40 ሚሊዮን ብር በላይ ግምት ያለው የምግብ ድጋፍ አደረገ።
የድርጅቱ የክብር አምባሳደር አትሌት ሃይሌ ገብረስላሴ በድጋፍ ርክክብ ስነ ስርአት ላይ እንዳሉት አሸባሪው ህወሓት አገር ለማፍረስ አልሞ የከፈተውን ጦርነት የአፋር ህዝብ መክቶ አገሩን አስከብሯል።
"የአፋር ህዝብ የሽብር ቡድኑ የለኮሰውን ጦርነት በመመከት አገር ወዳድነትና ጀግንነቱን በተግባር ማሳየቱን ገልጾ፣ በጦርነቱ የተጎዱ ወገኖችን ለመደገፍና የወደሙ መሠረተ ልማቶችን ለመጠገን በሚደረገው ጥረት ድርጅቱ የበኩሉን እንደሚወጣ አስታውቋል።
የሰዎች ለሰዎች በጎ-አድራጎት ድርጅት የኢትዮጵያ ተጠሪ አቶ ይልማ ታዩ በበኩላቸው ድርጅቱ በክልሉ የተለያዩ አካባቢዎች የሚገኙ ተፈናቃዮች የሚገኙበትን ሁኔታ ተዘዋውሮ በመመልከት የወገኖችን የድጋፍ ሁኔታ መለየቱን ተናግረዋል ።
"በልየታው መሰረት ከ40 ሚሊዮን ብር በላይ ግምት ያላቸው ምግቦችን ዛሬ ድጋፍ አድርጓል" ብለዋል።
አቶ ይልማ እንዳሉት ከተደረገው ድጋፍ ውስጥ ዱቄት፣ ሩዝ፣ የምግብ ዘይትን ጨምሮ የተለያዩ የሕጻናት አልሚ ምግቦች ይገኙበታል።
ድጋፉ ለ40 ሺህ ሰዎች የአንድ ወር ቀለብ እንደሚሆን የገለጹት አቶ ይልማ ድርጅቱ በቀጣይም በክልሉ በመልሶ ግንባታ ሥራዎች ላይ በንቃት በመሳተፍ የድርሻውን እንደሚወጣ አረጋግጠዋል።
በምክትል ርዕሰ መስተዳድ ማዕረግ የአፋር ክልል የኢኮኖሚ ክላስተር አስተባባሪ አቶ አሊ ሁሴን ድርጅቱ ያደረገው ድጋፍ የክልሉ መንግስት ለተጎጂዎች እያደረገ ያለውን ሰብአዊ እርዳታ የሚያግዝ መሆኑን አመልክተዋል።
ለድጋፉ በክልሉ መንግስትና ህዝብ ስም አመስግነው ጅርጅቱ በወደሙ ተቋማት መልሶ ግንባታ ላይ የነቃ ተሳትፎ እንሚያደርግ ያላቸውን እምነት ገልጸዋል።