ኢትዮጵያ በውጭ የሚኖሩ የተማሩ ዜጎቿን በዘላቂነት መጠቀም የሚያስችላት አደረጃጀት ያስፈልጋታል - ኢዜአ አማርኛ
ኢትዮጵያ በውጭ የሚኖሩ የተማሩ ዜጎቿን በዘላቂነት መጠቀም የሚያስችላት አደረጃጀት ያስፈልጋታል
አዲስ አበባ ታህሳስ 23/2014 (ኢዜአ) ኢትዮጵያ በውጭ አገራት የሚኖሩ የተማሩ ዜጎቿን እንደ ትልቅ ሀብት ቆጥራ በዘላቂነት መጠቀም የሚያስችላትን አደረጃጀት በየአገራቱ ኤምባሲዎች ልትዘረጋ ይገባል ይላሉ እውቁ ትውልደ ኢትዮጵያዊ ኤሜሪተስ ፕሮፌሰር ጥላሁን ይልማ።
ፕሮፌሰሩ አያይዘውም አሸባሪው የህወሓት ቡድን ለኢትዮጵያ ነቀርሳ በመሆኑ እስከ ወዲያኛው መነቀል አለበት ሲሉ ተናግረዋል።
ኤሜሪተስ ፕሮፌሰር ጥላሁን ይልማ፤ በአሜሪካ ካሊፎርኒያ ዳቪስ ዩኒቨርሲቲ በሰወና በእንስሳት ላይ ለሚከሰቱ በሽታዎች በዘረመል ምህንድስ፣ ክትባትና ሕክምና ዘርፍ የሚያጠኑ የሳይንስ ሊቅ ናቸው።
ትውልደ ኢትዮጵያዊው ሳይንቲስት ከመቶ ዓመት በፊት በአውሮጳና በአፍሪካ ከፍተኛ ዕልቂት ላደረሰው 'ደስታ' የተሰኘ የከብቶች በሽታ /Rinderpest/ መከላከያ ክትባት ግኝታቸው በዓለም አቀፍ ደረጃ አንቱ ተብለዋል።
በአውሮጳዊያኑ አቆጣጠር ከ1980-2006 በተማሩበት ካሊፎርኒያና በዋሽንግተን ስቴት ዩኒቨርሲቲዎች ከረዳት እስከ ሙሉ ፕሮፌሰርነት ማዕረግ ያገለገሉት ፕሮፌሰሩ፤ እ.አ.አ ከ2017 ወዲህ ልዩ ወይም 'ዲስቲንጉሽድ' ፕሮፌሰር የተባሉ ብቸኛው ኢትዮጵያዊም ናቸው።
ከ124 በላይ የሚሆኑ የምርምር ግኝቶች በስመጥር ዓለም አቀፍ የምርምር መጽሔቶች ያሳተሙት ፕሮፌሰሩ፤ የበርካታ የሳይንስ አካዳሚዎች አባልና ዓለም አቀፍ ሽልማቶችን ተቀዳጅተዋል።
"በኢትዮጵያ ጉዳይ ሕይወቴን እሰጣለሁ" የሚሉት እኒህ ጉምቱ ሳይንቲስት፤ አሸባሪው ህወሓት ወደ ስልጣን እንደወጣ በኢትዮጵያ ታሪካዊ ጠላቶች የሚጋለብ ጸረ-ኢትዮጵያ ስብስብ መሆኑን ሞግተው ነበር።
ከ1980ዎቹ አጋማሽ ጀምሮ የትህነግ ቡድን ኢትዮጵያዊያንን በዘር ከፋፍሎ አገሪቷን ለመዝረፍና ለማዳከም የተነሳ ወንበዴና ዘረኛ ስብስብ እንደሆነ በተከታታይ በርካታ አርቲክሎችን ጽፈዋል።
ይልቁንም ለአገር ሕልውና ስጋት የሆነው የአሸባረውን ቡድን ክፋት ስልጣን ላይ ከወጣበት ጊዜ ጀምሮ ስለተገለጠላቸው በዓለም አቀፍ ሚዲያዎች ለአብነትም በኒውስ ዊክ፣ ኒውዮርክ ታይምስ ጋዜጦኝ ሞግተዋል።
ዛሬም ቢሆን በሚችሉት ሁሉ ለአሜሪካ መንግስት የሕዝብ እንደራሴዎች ስለ አገራቸው ዕውነቱን በማስረዳት በኢትዮጵያ ላይ የሚደረገው ኢ-ፍትሃዊ ጣልቃ ገብነት እንዲቆም እየወተወቱ ነው።
ፕሮፌሰር ጥላሁን በግላቸው ከቻይና ሳይንቲስቶች ጋር ግንኙነት በመፍጠር አሜሪካን ያስቆጣውን የአፍሪካ በሽታ መከላከልና መቆጣጠር ማዕከል /ሲዲሲ/ን ጨምሮ በኢትዮጵያ የሕክምናና የምርምር ማዕከላት በአዲስ አበባ እንዲገነባም ትልቅ ሚና ተጫውተዋል።
ከሶስት አስርት ዓመታት በፊት ወያኔ ለኢትዮጵያ ካንሰር በመሆኑ መወገድ እንዳለበት ብሞግትም፤ ሰሚ አላገኘሁም ነበር፤ አሁንም ግን አልረፈደም ይህ ነቀርሳ መነቀል አለበት ይላሉ ፕሮፌሰር ጥላሁን ይልማ።
አሁንም ወያኔ ስር መሰረቱ እንደ ካንሰር ካልተነቀለ ስጋት ስለሚሆን በየትኛውም አይነት ዘዴ ይህን እኩይ ቡድን ማጥፋት ተገቢ ነው ብለዋል።
ኢትዮጵያ ወያኔን መሰል ባንዳ በመጠቀም ምዕራባዊያን ባያሴሩባት ኖሮ ዛሬ እንደ ደቡብ ኮሪያና ታይዋን ትልቅ ደረጃ ላይ ትደርስ ነበር የሚል እምነት አላቸው።
ምዕራባዊያን አፍሪካዊያንን በማበጣበጥ የተማሩትን ወደ አገራቸው ወስደው መጠቀም ዓላማቸው መሆኑን የገለጹት ፕሮፌሰሩ ለዚህ ማሳያም ራሳቸውን ይጠቅሳሉ።
በየዓለም ማዕዘናቱ የተበተኑ የኢትዮጵያ ልጆች ምቹ ሁኔታ ተፈጥሮላቸው በኢትዮጵያ ምርምር ማካሄድ ቢችሉ ትልቅ አገራዊ ለውጥ እንደሚኖርም ይገልጻሉ።
ማንዴላን መሰል ታጋዮች ባሰለጠነችው ኢትዮጵያ ላይ አፓርታይድ መሰል ስርዓት የተከለውን ወያኔን በማጥፋት በአንድ ሰንደቅ ኢትዮጵያዊያንን በሕብረት የሚያኖር ስርዓት ያስፈልጋል ነው ያሉት።
መንግስት ኢትዮጵያዊያን በፍቅርና በመተሳሰብ የሚንኖሩበት፣ ባህላቸውን የሚያጎለብቱበት፣ ዜጎች በነጻነት ተንቀሳቅሰው የሚሰሩብትን ስርዓት ሊገነባ ይገባል ብለዋል።
ኢትዮጵያ በወቅቱ የገጠማትን ችግር ለመቋቋም በውጭ የሚኖሩ ኢትዮጵያዊያንና ትውልደ ኢትዮጵያዊያን አገራቸውን ምን ያህል እንደሚወዱ ያስመሰከሩበት የሚያኮራ ትልቅ ንቅናቄ ነው ብለዋል።
የኢትዮጵያዊያኑ ንቅናቄም በርካታ አፍሪካዊያን ሆ ብለው ተነስተው ኢትዮጵያን ሲደግፉ የተስተዋለበትና አፍሪካን ያነሳሳ ሁነት ነው ብለውታል።
ዳያስፖራው በተለይም በተለያዩ ዘርፎች ከፍተኛ ትምህርት ያላችው ምሁራን የኢትዮጵያን ሁለንተናዊ እድገት እንዲደግፉ የኢትዮጵያ መንግስት እንደ ትልቅ ሃብት ሊመለከተውና ሊተኮርበት ይገባል ብለዋል።
ከዚህም የዳያስፖራውን አስተዋጽኦ በዘላቂነት ለመጠቀም በተለይም በአውሮፓ እና በአሜሪካ ኤምባሲዎች ለዳያስፖራው ልዩ አገልግሎት መስጫ የአሰራር ስርዓቶች ሊዘረጉና ሊሰራ ይገባል ነው ያሉት።