ጠቅላይ ሚኒስትር አቢይ አህመድ በመጪው የአፍሪካ ሕብረት ስብሰባ አዲስ አንቀጽ ይዘው መቅረብ አለባቸው - ኢዜአ አማርኛ
ጠቅላይ ሚኒስትር አቢይ አህመድ በመጪው የአፍሪካ ሕብረት ስብሰባ አዲስ አንቀጽ ይዘው መቅረብ አለባቸው
አዲስ አበባ፤ ታህሳስ 23 ቀን 2014 (ኢዜአ) ጠቅላይ ሚኒስትር አቢይ አህመድ በመጪው የመሪዎች ስብሰባ አፍሪካን ከምዕራብ ዘመም ዘረፋ፣ ወረራና ሽብር ለመከላከል ለኅብረቱ አዲስ አንቀጽ ማቅረብ አለባቸው ሲሉፕሮፌሰር ጥላሁን ይልማ ገለጹ።
የኢትዮጵያን ሕልውና ለማረገገጥ ያለማንም ፈቃድ በፈለግነው መንገድ የሚከላከለው የኢትዮጵያ ሕዝብ ብቻ ነው ሲሉም ተናግረዋል።
ኤሜሪተስ ፕሮፌሰር ጥላሁን ይልማ ምዕራባዊያን በቀለም ላይ ተመስርተው የሚያሳድሩትን የዘረኝነት ጫና ተቋቁመው ለስኬት የበቁ፤ በአሜሪካ ካሊፎርኒያ ዳቪስ ዩኒቨርሲቲ ዲስቲንጉሽንድ ፕሮፌሰር የተሰኙ ናቸው።
እኒህ ፕሮፌሰር ምዕራባዊያን በአፍሪካ ላይ ስውር ዓላማዎች እንዳሏቸው ይገልጻሉ።
እነሱም የነጭ ሕዝብን የዘር የበላይነት ማስቀጠል፣ የጥቁሮችን ባህላዊና ተፈጥሯዊ ሀብት መበዝበዝ እና አፍሪካ ሕዝቧን ከመለወጥና አቅሟን ከመገንባት ፈንታ በጦርነት አተራምሶ የጦር መሳሪያ መሸጥ ናቸው።
በአፍሪካ አገራት የእርስ በእርስ ጦርነትና እልቂት ከፈጠሩ በኋላ ደግሞ ከደሃ አገራት የተማሩ ሰዎችን በመውሰድ በአገራቸው ማሰራት፣ አገራታቸውን ማበልጸግ ዓላማቸው መሆኑን አፍጋኒስታንን አብነት ያነሳሉ።
አፍጋኒስታንን ፍርስርሷን ካወጡና ከዘረፏት በኋላ ከ200 ሺህ በላይ ምሁራንን ወደ አገራቸው ወስደዋል ሲሉ የአሜሪካን የኒዮኮሎኒያሊዝም ስልት ይጠቅሳሉ።
በኢትዮጵያም በአድዋ ድል ቂም በመያዝ ባህልና ታሪኳን አጥፍተው የተቀረውን አፍሪካ መቀራመት እንደሚሹ ገልጸው፤ ኢትዮጵያ ላይ የሚያደርጉት አሁናዊ ጫናም የዚህ ሴራ አካል ነው ብለዋል።
አንዳንድ ምዕራባዊያን ኢትዮጵያን በዘር ከፋፍለው ለመበዝበዝ የኢትዮጵያን ፊደል ለማጥፋት፣ የጋራ ቋንቋ እንዳይኖር ለማድረግና ስነ ልቦናችውን ለመስበር ስርዓተ ትምህርት ቀርጸው ከህወሓት ጋር ሲሰሩ እንደነበር ስውር ሰነዶችን ማግኘታቸውን ገልጸዋል።
ኢትዮጵያዊያንም የአገራቸውን ሕልውና የሚጎዱ የአንዳንድ ምዕራባዊያን አገራት ጫናዎችን በተለይም የአሜሪካና እንግሊዝን የተሳሳተ አካሄድ መከላከል እንደሚገባቸው አሳስበዋል።
የኢትዮጵያን ሕልውና ለመከላከል በፈለግነው መንገድ እንችላለን፤ የኢትዮጵያን ሕልውና ለማረጋገጥ የሚወስነውም የኢትዮጵያ ሕዝብ ብቻ ነው ብለዋል።
በእንግሊዝና በአሜሪካ የምርምር ተቋማት በኢትዮጵያ በዘረመል ምህንድስና ባዮቴክኖሎጂን ምርምርን በአፍሪካዊያን ለማስፋፋት ጥረት ቢያደርጉም ጥቁሮች ከእኛ ምርት መጠቀም እንጂ ይህን ጥበብ ማወቅ የለባቸውም ብለው እንዳልተባበሯችው በራሳቸውን ላይ የደረሰውን በዋቢነት ይጠቅሳሉ።
በዚህም በዓለም ላይ አሉ ከተባሉ የቻይና ሳይንቲስቶች ጋር ግንኙነት በመፍጠር በኢትዮጵያና በአፍሪካ የሳይንስ ምርምሮች እንዲስፋፉ ማድረጋቸውን፤ ለአብነትም በአዲስ አበባ የጉበትና ኩላሊት መመርመሪያ ማዕከልን አንስተዋል።
ኢትዮጵያም እንደ አገር ከምዕራባዊያን ባለፈ በአፍሪካ ላይ በመሰረተ ልማት ቻይናን መሰል አገራት ጋር ትስስሯን እንድታጠናክር መክረዋል።
ኢትዮጵያም ሆነ የተቀረው አፍሪካ ግንኙነቱን ከቻይና እና መሰል ሃያላን አገራት ጋር በማድረግ የምዕራብ ዘመም ጫናን መቋቋም እንዳለበትም ነው የገለጹት።
ቻይና በኢትዮጵያ በሁሉም መሰረተ ልማት መስኮች ከፍተኛ ኢንቨስትመንት እያካሄደች መሆኑን በማውሳት፤ ቻይና ለራሷ ኢንቨስትመንት ስትል ከኢትዮጵያ ጎን እንደምትቆም እምነታቸውን ገልጸዋል።
ከሁለት ዓመታት በፊት በአፍሪካ ሕብረት ጥሪ ተደርጎላችው ንግግር ማድጋቸውን ያወሱት ፕሮፌሰር ጥላሁን፤ አፍሪካ በራሷ ማንነት እንድትኮራና እንድትጠቀም አማርኛ ፊደልን በምሳሌነት አንስተው ማስረዳታቸውን ገልጸዋል።
የአፍሪካ አንድነት በአዲስ አበባ ከመመስረቱ ባለፈ አገራቱ በፓን አፍሪካዊነት መንፈስ አንድ ሆነው የምዕራባዊያንን ጠላቶች የሚቋቋሙበት አንቀጽ በሕግ ሊያጸድቁ ይገባል ነው ያሉት።
ለዚህም በመጪው የመሪዎች ስብሰባ ጠቅላይ ሚኒስትር አቢይ አህመድ ቀዳማዊ አጼ ኅይለስላሴ በፓን አፍሪካዊነት እንደነበራቸው ሚና ሁሉ ሃሳቡን ይዘው የመሪነትና ማስተባበር ሚናቸውን እንዲወጡ ጠይቀዋል።
ይህም አፍሪካዊያን ምዕራባዊያን የሚያደርጉትን ዘረፋ፣ ወረራና ሽብር ለመከላከል ያስችላል ብለዋል።
ኤሜሪተስ ፕሮፌሰር ጥላሁን ይልማ በአሜሪካ ካሊፎርኒያ ዳቪስ ዩኒቨርሲቲ በሰውና በእንስሳት ላይ ለሚከሰቱ በሽታዎች በዘረመል ምህንድስ፣ ክትባትና ሕክምና ዘርፍ የሚያጠኑ የሳይንስ ሊቅ ናቸው።
ከመቶ ዓመት በፊት በአውሮጳና በአፍሪካ ከፍተኛ ዕልቂት ላደረሰው 'ደስታ' የተሰኘ የከብቶች በሽታ ክትባት ማግኘትን ጨምሮ በእንስሳትና በሰው ሕክምናም በርካታ ግኝቶች ያሏቸው፤ ዓለም አቀፍ አንቱታን ያተረፉ ምሁር ናቸው።