አገረ-ስብከቱ ለተጎዱ የሰሜን ወሎ አካባቢ ወገኖች 1 ነጥብ 4 ሚሊዮን ብር ግምት ያለው የምግብ ቁሳቁስ ድጋፍ አደረገ - ኢዜአ አማርኛ
አገረ-ስብከቱ ለተጎዱ የሰሜን ወሎ አካባቢ ወገኖች 1 ነጥብ 4 ሚሊዮን ብር ግምት ያለው የምግብ ቁሳቁስ ድጋፍ አደረገ
ታህሳስ 23/2014(ኢዜአ) በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተ-ክርስቲያን የባህር ዳር አገረ ስብከት በሰሜን ወሎ ዞን ወልድያና አካባቢው በአሸባሪው ቡድን ጉዳት ለደረሰባቸው ወገኖች 1 ነጥብ 4 ሚሊዮን ብር ግምት ያለው የምግብ ቁሳቁስ ድጋፍ አደረገ፡፡
ድጋፉን የባህር ዳር አገረ ስብክት ሊቀ-ጳጳስ ብጹዕ አቡነ አብርሃም በወልድያ ከተማ በመገኘት ለብጹዕ አቡነ ኤርሚያስ አስረክበዋል፡፡
አቡነ አብርሃም የሰሜን እና የደቡብ ወሎ እንዲሁም የኦሮሞ ልዩ ዞን ሊቀ-ጳጳስ አቡነ ኤርሚያስ ሕዝቡ በአሸባሪው ቡድን ወረራ ውስጥ በነበረ ጊዜ ለሕዝቡ አለኝታ የሆኑ አባት በመሆናቸው ምስጋና አቅርበውላቸዋል፡፡
ሕዝቡን በሃይማኖት ሳይለዩ በእኩል በመመልከት በረሃብ እንዳይጎዳ ላደረጉት ተግባርም ምስጋና ቸረዋል።
በዚህ ተግባራቸው የቤተክርስቲያኗ እውነተኛ አባት በመሆን ሕዝቧን በመጠበቅ ቤተክርስቲያኒቷን ከፍ ማድረጋቸውንም ነው የገለጹት።
የባህር ዳር አገረ ስብከት በሰሜን ወሎ ጉዳት ለደረሰባቸው ወገኖች ባደረገው የምግብ ቁሳቁስ ድጋፍ ዱቄት፣ ዘይት፣ ጤፍ እና የህጻናት ምግቦች ይገኙበታል።
ብጹዕ አቡነ ኤርሚያስ ለተደረገው ድጋፍ በተለይም የህጻናት ማሳደጊያን ከግምት በማስገባት ለእነርሱ የሚሆን ምግብ ይዘው በመምጣታቸው ምስጋና አቅርበዋል።
በአሸባሪው ቡድን ወረራ በመከራ ውስጥ በነበሩበትም ሆነ አሁን በርካታ የሚያስደስቱ ኢትዮጵያዊያን መኖራቸውን ተመልክተናል ብለዋል ብፁዕነታቸው።
በችግር ቀን ተደጋግፎ ማለፍን፣ አለመሰሰትን፣ አካፍሎ መስጠትንም ያየንበት በመሆኑ ብዙ ተምረንበታል ብለዋል፡፡
በአሸባሪው ቡድን የመጡ መከራዎች ብዙ ቢሆኑም በወገን ያየነው ኅብረት፣ አንድነትና መተሳሰብ አስደስቶናል ሲሉ ነው የገለጹት።
የባህር ዳር አገረ ስብከት ከዚህ ቀደምም በተለያዩ አካባቢዎች ጉዳት ለደረሰባቸው ወገኖች ድጋፍ ሲያደርግ መቆየቱ ተገልጿል፡፡
በተያያዘ ዜና የኢትዮጵያ የሃይማኖት ተቋማት ጉባኤ በሰሜን ወሎ ለሚገኙ ወገኖች የተለያዩ ምግብ ነክ ድጋፎችን አበርክቷል።
በድጋፍ ርክክቡ መርሃ ግብር ከሁሉም የእምነት ተቋማት የተውጣጡ የሃይማኖት አባቶች ተገኝተዋል፡፡
የኢትዮጵያ የሃይማኖት ተቋማት ጉባኤ በሰሜን እና ደቡብ ወሎ ዞኖች ከ6 ሚሊዮን ብር በላይ ግምት ያለው የምግብ ነክ ቁሳቁሶችን ድጋፍ አድርጓል፡፡