ዳያሥፖራው በአሸባሪው የጥፋት ቡድን የደረሰውን ጉዳት መልሶ ለመገንባት በቋሚነት እንዲደግፍ ጥሪ ቀረበ - ኢዜአ አማርኛ
ዳያሥፖራው በአሸባሪው የጥፋት ቡድን የደረሰውን ጉዳት መልሶ ለመገንባት በቋሚነት እንዲደግፍ ጥሪ ቀረበ
ታህሳስ 23 ቀን 2014 (ኢዜአ) ኢትዮጵያውያንና ትውልደ ኢትዮጵያውያን ዳያስፖራው አሸባሪው ህወሓት ኢትዮጵያ ላይ ያደረሰውን ጉዳት መልሶ ለመገንባት በቋሚነት እንዲደግፍ በጀርመን የኢፌዲሪ ባለሙሉ ስልጣን አምባሳደር ሙሉ ሰሎሞን ጥሪ አቀረቡ፡፡
በጀርመን የኢትዮጵያ ኤምባሲ ከሚሸፍናቸዉ በስዊድን፣ ፖላንድ፣ ኖርወይ፣ ዴንማርክ እና ፊንላንድ ከሚገኙ ኢትዮጵያውያን እና ትዉልደ ኢትዮጵያውያን ጋር በ"ኢትዮጵያውያን ለኢትዮጵያ" ማህበር አስተባባሪነት በሀገራችን ወቅታዊ ጉዳይና የተጎዱ ወገኖችን በቀጣይነት ለመደገፍ የሚቻልበት ሁኔታዎች ላይ ውይይት ተደርጓል።
በውይይትም በጀርመን የኢ.ፌ.ዲ.ሪ ልዩ መልዕክተኛና ባለሙሉ ስልጣን አምባሳደር ሙሉ ሰሎሞን በወቅታዊ የአገራችን ጉዳይ ላይ ሰፊ ማብራሪያ የሰጡ ሲሆን ቀጣይነት ባለዉ መልኩ ከእናት አገራቸዉ ኢትዮጵያ ጎን እንዲቆሙ እና በቋሚነት መንገድ ወገኖቻቸዉን እንዲደግፉ ጥሪ አቅርበዋል።
ለሀገራዊ ጥሪ አፋጣኝ ምላሽ በመስጠት የውይይት መድረኩን ያስተባበሩት አካላትንም አመስግነዋል፡፡
በመድረኩ ላይ በስዊድን ስቶኮልም የሚኖሩ ዶክተር ሙሉነህ አሸባሪው የጥፋት ቡድን በኢትዮጵያ ላይ ያደረሰውን ጉዳትና እንዴት መመከት አለብን የሚለዉን አስመልክተው የራሳቸውን ምልከታ አቅርበዋል።
በመጨረሻም በቀረበው ገለጻ ላይ ውይይት የተደረገ ሲሆን በቀጣይም የተጎዱ ወገኖቻችን በቋሚነት ለመደገፍ ስለሚደረገው እንቅስቃሴ እና ዳያስፖራዉ ከኤምባሲው ጋር ተቀራርቦ ለመስራት የሚያስችሉ ጥያቄዎች ቀርበው ምላሽ መሰጠቱን ከውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ቃል አቀባይ ጽህፈት ቤት የተገኘው መረጃ ያመለክታል።