የሶማሌ ክልል ፕሬዝዳንት የነበሩት አብዲ መሐመድ ኡመር በቁጥጥር ስር ዋሉ - ኢዜአ አማርኛ
የሶማሌ ክልል ፕሬዝዳንት የነበሩት አብዲ መሐመድ ኡመር በቁጥጥር ስር ዋሉ
አዲስ አበባ ነሓሴ 21/2010 የሶማሌ ክልል ፕሬዝዳንት የነበሩት አብዲ መሐመድ ኡመር በቁጥጥር ስር ዋሉ። በቁጥጥር ስር ሊውሉ የቻሉት የሰብዓዊ መብት ጥሰት፣ የብሄር ግጭት፣ በኃይማኖት መካከል ግጭት እንዲፈጠር ማድረግና ሌሎችም ወንጀሎችን ፈፅመዋል ተብለው ነው። ፖሊስ እርሳቸውን ጨምሮ በተመሳሳይ ድርጊት ተሳትፈዋል የተባሉ ሌሎችን በቁጥጥር ስር እያዋለ መሆኑን ነው ጠቅላይ አቃቤ ህግ ያስታወቀው። ፌዴራል ፖሊስ በቁጥጥር ስር ያዋላቸው አዲስ አበባ አትላስ አካባቢ ካለው መኖሪያ ቤታቸው መሆኑንም ለማወቅ ተችሏል። አራት ሽጉጥና አምስት ክላሽም ከቤታቸው መገኘቱ ነው የተገለጸው። የኢትዮጵያ ሶማሌ ክልል ምክር ቤት በትናንትናው ዕለት ባካሄደው አስቸኳይ ስብሰባ የሰባት የምክር ቤት አባላትን ያለመከሰስ መብት ማንሳቱ ታውቋል። የምክር ቤት አባላት ያለመከሰስ መብት ካነሳባቸው አንዱ የክልሉ የቀድሞው ፕሬዝዳንት አቶ አብዲ መሐመድ ኡመር ሲሆኑ መብታቸው የተነሳው በክልሉ ተፈጥሮ ከነበረው ሁከት ጋር በተያያዘ ወንጀል በመጠርጠራቸው መሆኑንም ምክር ቤቱ አስታውቋል። የአባላቱን ያመለከሰስ መብት የማንሳት ውሳኔውንም ምክር ቤቱ በሙሉ ድምጽ እንዳፀደቀው ነው የተገለፀው።