የኢትዮጵያ የውጭ ግንኙነት ላይ ያተኮረ መጽሃፍ ለንባብ በቃ

አዲስ አበባ፣ ታህሳስ 22/2014(ኢዜአ)  "የኢትዮጵያ የውጭ ግንኙነት ከጥንት እስከዛሬ" የሚል ርዕሰ ያለውና ትኩረቱን በኢትዮጵያ የውጭ ግንኙነት ላይ ያደረገ መጽሃፍ ለንባብ በቃ።

የመጽሃፉ ፀሃፊ በውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር የአፍሪካ ጉዳዮች ዳይሬክተር ጄኔራል አምባሳደር አክሊሉ ከበደ ናቸው።

በመጽሃፉ የምረቃ ሥነ-ሥርዓት አምባሳደር ዲና ሙፍቲ እና አምባሳደር ምህረተአብ ሙሉጌታን ጨምሮ የጸሃፊው ቤተሰቦች ታድመዋል።  

የኢትዮጵያ የውጭ ጉዳይ ፖሊሲ፣ በየዘመኑ የነበሩ ግንኙነቶች፣ ብሔራዊ ደህንነት፣ ዓለም አቀፍ ንግድ፣ ኢንቨስትመንት እና ቱሪዝም ላይ ትኩረቱን ያደረገው መጽሃፉ በ343 ገጾች ተቀንብቧል።

በተለይ ጥናትና ምርምር ለሚያካሂዱ በግብዓትነት ከማገልገሉ ባሻገር ዲፕሎማሲውን በማጠናከር ረገድ ያለው ፋይዳም ከፍ ያለ እንደሚሆን ተነግሯል።

የመጽሃፉ ጸሃፊ አምባሳደር አክሊሉ ከበደ በተለይ ለኢዜአ እንዳሉት፤ ኢትዮጵያ በሺህዎች የሚቆጠር የውጭ ግንኙነት ታሪክ ቢኖሯትም በታሪኳ ልክ በአግባቡ የተሰነደ መጽሃፍ በገበያ ላይ ብዙ አይታይም።    

መጽሃፉን ለመጻፍ የተነሳሳሁትም ይህን ክፍተት ለመሙላት በሚደረገው ጥረት የበኩሌን ለመወጣት ነው ሲሉ ነው የተናገሩት።   

ታሪክን ማወቅ ወደፊት ለመንደርደር ጠቃሚ ያሉት አምባሳደር አክሊሉ መጽሃፉ ቀጣይ የዲፕሎማሲ ስራዎችን የሚያግዝ ይሆናል ብለዋል።  

ከመጽሃፉ ሽያጭ ከሚገኘው ገቢ 60 በመቶው በጦርነቱ ሳቢያ ጉዳት ለደረሰባቸው ዜጎች መቋቋሚያ እንዲሆን መደረጉንም ገልጸዋል።   

ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትርና የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ደመቀ መኮንንን ወክለው ንግግር ያደረጉት አምባሳደር ምህረተአብ ሙሉጌታ፤ አምባሳደር አክሊሉ ከመደበኛ ሥራቸው ጎን ለጎን ብዙ ድካም የፈሰሰበትን መጽሃፍ ለንባብ በማብቃታቸው ዓርአያ መሆን እንደቻሉ ገልጸዋል።

ልምድ ያላቸው ዲፕሎማቶች ልምዳቸውን ማጋራት ይጠበቅባቸዋል፤ አምባሳደር አክሊሉ በዚህ ረገድ ያከናወኑት ተግባር የሚያስመሰግናቸው ነው ብለዋል።

አምባሳደር አክሊሉ ከዚህ ቀደምም በሕንድ የነበራቸውን ቆይታ መሰረት በማድረግ "ይህችን አገር እንዳየኋት" የሚል መጽሃፍ ለንባብ አብቅተዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም