ወደ አማራ ክልል የሚመጡ ዳያስፖራዎች ያለ ስጋት እንዲንቀሳቀሱ አስፈላጊው ዝግጅት ተደርጓል

69

ባህር ዳር፣  ታህሳስ 22/2014 ( ኢዜአ) የጠቅላይ ሚኒስትሩን ወደ ሀገር ቤት ጥሪ ተከትሎ የገናና የጥምቀት በዓላትን ለማክበር ወደ አማራ ክልል የሚመጡ ዳያስፖራዎች በሁሉም አካባቢዎች ያለስጋት እንዲንቀሳቀሱ አስፈላጊውን የፀጥታ ዝግጅት መደረጉን የክልሉ የሰላምና ፀጥታ ቢሮ አስታወቀ።

የቢሮው የህዝብ ግንኙነት ኃላፊ አቶ እንግዳው ጠገናው ለኢዜአ እንዳሉት ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር ዐቢይ አህመድ ባቀረቡት ጥሪ መሰረት በርካታ ኢትዮጵያዊያንና ትውልደ ኢትዮጵያዊያን ወደ አገር ቤት እየገቡ ነው።

ገናን በላል ይበላ፣ ጥምቀትን በጎንደር ለማክበር ወደ አማራ ክልል ለሚመጡ እንግዶችም አስተማማኝ የፀጥታ ጥበቃ ለማድረግ የሚያስችል የዝግጅት ሥራ መጠናቀቁን ገልፀዋል።

ዳያስፖራዎች በርካታ ጫናዎችን ተቋቁመው የመጡበትን ዓላማ አሳክተው እንዲመለሱ ለማድረግ የሰላምና ደህንነት ስራዎች ቀድመው መሰራታቸውን አመልክተዋል።

የፀጥታ ሥራው እየተሰራ ያለው ከፌዴራልና ከክልል የፀጥታ አካላት ጋር በቅንጅት መሆኑን ጠቁመው፣ ዳያስፖራዎች በሄዱበት ቦታ ሁሉ ያለስጋት መንቀሳቀስ እንዲችሉ ታስቦ እየተሰራ መሆኑን ተናግረዋል።     

ኃላፊው እንዳሉት ወደ ክልሉ ለሚመጡ ዳያስፓራዎች የወቅቱን የፀጥታ ሁኔታ ግምት ውስጥ ባስገባ መልኩ ጥበቃ ለማድረግ ዝግጅቱ ተጠናቋል።

ከውጭ የሚመጡ ኢትዮጵያዊያንና ትውልደ ኢትዮጵያዊያን በክልሉ ውስጥ ከሚነሱባቸው ቦታዎች ጀምሮ እስከ ሚያርፉባቸው ሆቴሎች ድረስ አስተማማኝ ጥበቃ እንደሚደረግላቸው አመልክተዋል።

በፀጥታ ሥራው የህዝብና የበጎ ፈቃደኛ ወጣቶች አቅም ጭምር ጥቅም ላይ መዋሉን አቶ እንግዳው ገልጸዋል።

ከህግ አስከባሪ የፀጥታ አካላት ውጭ የትኛውም አካል ህጋዊ የጦር መሳሪያ ጭምር ይዞ መንቀሳቀስ በጥብቅ የተከለከለ መሆኑን አመልክተዋል።

አቶ እንግዳው እንዳሉት ዳያስፖራዎቹ በአሸባሪው የህወሓት ቡድን ጉዳት የደረሰባቸውን አካባቢዎች ጎብኝተው የወደሙ ተቋማትን መልሶ በመገንባት ሂደት የራሳቸው ሚና ይኖራቸዋል።  

በመሆኑም ህዝቡ በህልውና ዘመቻው በደጀንነት አስተዋጾ እንዳደረገው ሁሉ ወደ ክልሉ ለሚመጡ ዳያስፖራዎች በወግና ባህሉ መሰረት ተቀብሎ እንዲሸኝ ጥሪ አቅርበዋል።

በተጨማሪ ከፀጥታ ኃይሉ ጎን በመሆን ህገ-ወጦችን ለመቆጣጠር በሚደረገው ሂደት መረጃ በመስጠት ማገዝ እንዳለበት አሳስበዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም