በኦሮሚያ ከበጋ መስኖ እርሻ 17 ሚሊዮን ኩንታል ስንዴ ለማምረት ታቅዶ እየተሰራ ነው

ታህሳስ 22 ቀን 2014 (ኢዜአ)  የኦሮሚያ ክልል በበጋ መስኖ እርሻ 350 ሺህ ሄክታር መሬትን በማልማት 17 ሚሊዮን ኩንታል ስንዴ ለማግኘት አቅዶ እየሰራ መሆኑን ገለፀ።

በክልሉ ግብርና ቢሮ ኃላፊ የተመራ ቡድን በደቡብ ምዕራብ ሸዋ ዞን ኢሉና በቾ ወረዳ የበጋ መስኖ እርሻ ስራን ጎብኝቷል።

የቢሮ ኃላፊው አቶ አበራ ወርቁ ክልሉ በመስኖ ለሚለማው የስንዴ እርሻ ልዩ ትኩረት ሰጥቷል ይላሉ።

በክልሉ ከዚህ ቀደም በስንዴ እርሻ የማይታወቁ አካባቢዎች ጭምር ወደ መስኖ ስራ እንዲገቡ እየተደረገ መሆኑንም ገልፀዋል።

ጅማ፣ ኢሉ አባቡር፣ ቡኖ በደሌን በመሳሰሉ ስንዴ አምራች ያልሆኑ አካባቢዎች የመስኖ እርሻ እየተካሔደ መሆኑን ጠቅሰዋል።

ክልሉ በአገር አቀፍ ደረጃ የስንዴ ፍጆታን ለመሸፈን፣ ሰፊ የስራ ዕድል ለመፍጠርና የአርሶ አደሩን የስራ ባህል ለመቀየር ያለሙ ስራዎችን እያከናወነ ነው ብለዋል።

በአሁኑ ወቅት በበጋ መስኖ እርሻ 350 ሺህ ሔክታር መሬት በስንዴ ምርት ለመሸፈን እየተሰራ ሲሆን ከዚህም 17 ሚሊዮን ኩንታል ስንዴ ለማግኘት መታቀዱንም ነው ኃላፊው የተናገሩት።

በእስካሁን ሂደትም ከ240 ሺህ ሄክታር በላይ መሬት በስንዴ መሸፈኑን ጠቁመዋል።

የደቡብ ምዕራብ ሸዋ ዞን ዋና አስተዳደሪ አቶ ታዬ ጉዲሳ በበኩላቸው በዞኑ በልዩ ሁኔታ የመስኖ ስራ እየተካሔደ መሆኑን ገልጸዋል።

በዞኑ የሚገኙ የተወሰኑ ወረዳዎች የአዋሽ ወንዝ በክረምት በሚያስከትለው ሙላት ምክንያት የግብርና ስራ ሳይሰሩ የሚያልፉ እንደሆኑም ተናግረዋል።

በመሆኑም አርሶ አደሩ በክረምቱ ያመለጠውን የግብርና ስራ ማካካስ እንዲችል በዞኑ ከ14 ሺህ ሄክታር መሬት በላይ ማሳ ላይ በበጋ መስኖ እርሻ ስንዴን ለመዝራት እየተሰራ መሆኑን ተናግረዋል።

የዞኑ አርሶ አደሮችም ቢያንስ ከሄክታር 30 ኩንታል ስንዴ ለማግኘት አቅደው የግብርና ስራውን እያቀላጠፉት ይገኛሉ ብለዋል።

አርሶ አደሮቹ በበኩላቸው መንግስት የግብዓት አቅርቦት እያደረገላቸው መሆኑንና በስንዴ ምርት ላይ ተስፋ መጣላቸውን ተናግረዋል።

አርሶ አደሮቹ የውኃ መሳቢያ ፓምፕ ችግር እንዳለባቸው ገልጸው መንግስት ይህን ችግራችንን ይፍታልን ሲሉ ጠይቀዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም