በአማራና በአፋር ክልሎች በአሸባሪው ህወሓት የተጎዱ አካባቢዎች በዳያስፖራው ይጎበኛሉ

35

ታህሳስ 22 ቀን 2014 (ኢዜአ) በአማራና በአፋር ክልሎች በአሸባሪው የህወሓት ቡድን የተጎዱ አካባቢዎች ወደ አገር ቤት በገቡ የዳያስፖራ አባላት እንደሚጎበኙ የዳያስፖራ ኤጀንሲ ገለፀ።

በጉብኝት መርሃ ግብሩ መሰረት በሁለቱ ክልሎች ከታህሳስ 25 ጀምሮ የሚጎበኙ ስፍራዎች የተለዩ ሲሆን የክልሎቹ መንግስታትም ዝግጅት አድርገዋል።

ወደ አገር ቤት የገቡ ዳያስፖራዎች በመጪው ሰኞ የወደሙ መሰረተ ልማቶችን እንደሚጎበኙ የኤጀንሲው የዳያስፖራ ተሳትፎ ዳይሬክተር አቶ አውላቸው ማስሬ ገልፀዋል።

ለጉብኝቱ የጉዞ መርሃ ግብር እስካሁን እያንዳንዳቸው ከ50 ሰው በላይ የያዙ ቡድኖች ምዝገባ አካሂደዋል።

አፋር ክልልን የወከሉት አምባሳደር አሚን አብዱልቃድር፤ በክልሉ ከአንበጣና ከጎርፍ አደጋ ባሻገር አሸባሪው ህወሓት ወረራ በፈጸመበት ወቅት ያደረሰው ጥፋት ችግሩን በእንቅርት ላይ ጆሮ ደግፍ አድርጎታል ብለዋል።

በክልሉ 1 ነጥብ 3 ሚሊዮን ሕዝብ እርዳታ የሚሻ በመሆኑ ዳያስፖራው በአካል በመገኘት ተመልክቶ የድርሻውን እንዲወጣ ትልቅ ዕድል ይፈጥራል ነው ያሉት።

በመሆኑም ከመጪው ታህሳስ 25 እስከ 27 በክልሉ ዋና ከተማ ሰመራ ሲምፖዚም ይካሄዳል፤ በጦርነቱ የተጎዱ ወረዳዎችም የሚጎበኙ ይሆናል ሲሉ አስታውቀዋል።

በክልሉ ውድመት ከተፈጸመባቸው አካባቢዎች በተጨማሪ የቱሪስት መዳረሻዎችም ይጎበኛሉ ብለዋል።

ዳያስፖራው ተጎጂዎችን መልሶ በማቋቋም ተግባር ተሳትፎውን ለማረጋገጥ በሚያስችል ደረጃ እንግዶችን ለመቀበል በቂ ዝግጅት መደረጉን ተናግረዋል።

አምባሳደር አሚን አሸባሪው ህወሓት ኮሪደሮችን ለመያዝ  በማለም ያደረሰው ጥቃት ከባድ ጉዳት ማስከተሉን ገልጸው፤ ዳያስፖራው ጉዳቱን በአካል ተገኝቶ መመልከቱ በመልሶ ግንባታው ትልቅ ተሳትፎ እንደሚጠበቅባቸው እንዲገነዘቡ ያስችላል ብለዋል።

የአማራ ክልልን የወከሉት አቶ ያየህ አዲስ በበኩላቸው ከፍተኛ ውድመት ያስተናገደው ክልሉ ወደ አካባቢው የሚጓዙ እንግዶችን ለማስተናገድ በቂ ዝግጅት አድርጓል ብለዋል።

ለዚህም በአዲስ አበባ ኮሚቴ አዋቅሮ የአቀባበሉን መርሃ ግብር እያስኬደ መሆኑን ነው የገለጹት።

በወጣው መርሃ ግብር መሰረት ከሸዋ እስከ ወልድያ፣ ከወልድያ እስከ ባሕር ዳር፣ ከጎንደር እስከ ማይካድራ  ወረራ የተፈጸመባቸው ቦታዎችና በጦርነቱ የደረሱ ውድመቶች ይጎበኛሉ።

እንዲሁም ገናን በላልይበላ እና ጥምቀትን በጎንደር አከባበር ክዋኔዎች፤ በክልሉ ከተሞችም ኤግዚቢሽንና ሲምፖዚየሞች እንደሚዘጋጁ ገልጸዋል።

የዳያስፖራ ምስጋና፣ አገራዊ አንድነትና የዳያስፖራው ሚና እንዲሁም የድህረ ጦርነት መልሶ ግንባታ ከተዘጋጁት መርሃ ግብሮች መካከል ተጠቃሽ ናቸው ብለዋል።

በአማራ ክልል ለሚደረጉ ጉብኝቶች የእንግዳ መቀበያ ቦታዎች የተዘጋጁ ሲሆን አስተማማኝ ፀጥታ እንዲኖር ከወዲሁ እየተሰራ እንደሆነም አክለዋል።

እንግዶች በክልሉ የተቋረጠውን የኢንተርኔት አገልግሎት እንዲያገኙ ከኢትዮ-ቴሌኮም ጋር ንግግር እየተደረገ መሆኑ ተገልጿል።

በተለይ ኮንፈረንስና ኤግዚቢሽን በሚካሄድባቸው አካባቢዎች የዳታ ኢንተርኔት ይከፈታል ተብሏል።

እንግዶች በሁለቱ ክልሎች መልሶ ግንባታ የሚኖራቸውን ሚናና የሚሳተፉባቸውን ፕሮጀክቶች በተመለከተ ስለደረሰው ውድመት ጥናት የተሰበሰበ በመሆኑ ከስራ ኃላፊዎች ጋር ምክክርና የመረጃ ልውውጥም ይኖራል።

ኢትዮጵያን እናልማ፣ እንገንባ፣ እንዘጋጅ‼

ሀገርን በዘላቂነት እናልማ‼

የፈረሰውን አብልጠን እንገንባ‼

ለማንኛውም ፈተና እንዘጋጅ‼

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም