በአሸባሪው ምክንያት በችግር ውስጥ የሚገኙ ዜጎችን ለመደገፍ አሁንም የኢትዮጵያዊያን ርብርብ ያስፈልጋል

77

ባህር ዳር፤ ታህሳስ 22 ቀን 2014 (ኢዜአ) በአማራ ክልል በሽብር ቡድኑ ወረራ ምክንያት በችግር ውስጥ የሚገኙ ዜጎችን ለመደገፍና በዘላቂነት ለማቋቋም በሚደረገው ጥረት አሁንም የኢትዮጵያዊያን ርብርብ እንደሚያስፈልግ የክልሉ መንግስት ኮሙዩኒኬሽን ቢሮ አስታወቀ።

የኢትዮጵያ ኢንቨስትመንት ኮሚሽን እና የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ሃይል በአማራ ክልል ለተፈናቀሉ ወገኖች 20 ሚሊየን ብር የጥሬ ገንዘብና  የዓይነት ድጋፍ ለክልሉ አስረክበዋል።

በዚህ ወቅት የቢሮ ሃላፊው አቶ ግዛቸው ሙሉነህ እንዳሉት፤አሸባሪው  የህወሃት  ቡድን በክልሉ በርካታ ዜጎችን ከቤት ንብረታቸው አፈናቅሏል፤ ንብረታቸውንም ዘርፏል።

የግልና የመንግስትን ንብረት ከመዝረፍና ከማውደም ባለፈ አርሶ አደሩ ምርቱን እንዳያመርትና የዘራውን ሰብልም እንዳይሰበስብ የሽብር ቡድኑ ወረራ በፈፀመባቸው አካባቢዎች ሲሰራ ቆይቷል።


በወራሪ ቡድን ምክንያት በአስቸጋሪ ሁኔታ ላይ ለሚገኙ ዜጎች ለማገዝ  የኢንቨስትመንት ኮሚሽንና የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ሃይል ተቋሞች ያደረጉት ድጋፍ  ከፍተኛ አስተዋፅኦ እንዳለው ገልጸዋል።

በሽብር ቡድኑ ጥቃት በችግር ውስጥ የሚገኙ ዜጎችን ለመደገፍና በዘላቂነት ለማቋቋም አሁንም የመላው ኢትዮጵያዊያን ርብርብ እንደሚያስፈልግ ነው ሃላፊው ያስታወቁት።

የአማራ ክልል አደጋ መከላከልና ምግብ ዋስትና ማስተባበሪያ  ኮሚሽነር አቶ ዘላለም ልጃለም በበኩላቸው፤ በሽብር ቡድኑ ወረራ ፈፅሞባቸው በነበሩ የክልሉ አካባቢዎች ከ11  ሚሊየን በላይ ዜጎች ድጋፍ እንደሚፈልጉ ገልጸዋል።

የሽብር ቡድኑ ወረራ በፈፀመበት ወቅትም ዜጎች ከቀያቸው እንዲፈናቀሉ አድርጓል ያሉት ኮሚሽነሩ ፤ይህም የዜጎችን ሃብትና ንብረት ከመዝረፍም ባለፈ እንዲወድም ማድረጉን አውስተዋል።

የኢንቨስትመንት ኮሚሽንና የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ሃይል ተቋማተ ዛሬ ያደረጉት ድጋፍ የተፈናቀሉ ወገኖችን ለመደገፍና ለማቋቋም ለሚደረገው ጥረት ትልቅ አስተዋፅኦ አለው ብለዋል።

የተደረገውን ድጋፍም ለተጎጂዎች በአግባቡ ተደራሽ እንዲሆን ኮሚሽኑ አበክሮ እንደሚሰራ ገልጸው፤ ሌሎች መሰል ተቋማትም ድጋፍ በማድረግ ለወገን ያላቸውን አጋርነት እንዲያሳዩም ጠይቀዋል።

አሸባሪው የህወሃት ቡድን በአማራና አፋር ክልል በፈፀመው ወረራ ምክንያት ከቤት ንብረታቸው ለተፈናቀሉ ወገኖች የተለያዩ ድጋፎችን ሲያደርጉ መቆየታቸውን የገለጹት ደግሞ የኢትዮጵያ ኢንቨስትመንት ኮሚሽን ምክትል ኮሚሽነር አቶ ዳንኤል ተሬሳ ናቸው።

በአሁኑ ወቅትም ኮሚሽኑ በኢትዮጵያ በኢንቨስትመንት የተሰማሩ የሃገር ውስጥና የውጭ ባለሃብቶችን በማስተባበር ያሰባሰቡትን 13 ሚሊየን ብር ግምት ያላቸው የምግብና የአልባሳት እንዲሁም የቤት ቁሳቁሶችን ለክልሉ አስረክበዋል።

በቀጣይም የተፈናቀሉ ወገኖችን መልሶ ለማቋቋም ለሚደረገው ጥረት ኮሚሽኑ ድጋፉን አጠናክሮ ይቀጥላል ብለዋል አቶ ዳንኤል።

''በወራሪውና በሽብር ቡድኑ የወደሙና ጉዳት የደረሰባቸውን የኢንቨስትመንት ተቋማት ፈጥነው ወደ ስራ እንዲገቡ እየተሰራ ነው'' ስሉ ተናግረዋል።

የኢትዮጵያ ኤሌክትራክ ሃይል ዋና ስራ አስፈፃሚ አቶ አሸብር ባልቻ ፤  የተቋሙ ሰራተኞችና አመራሮች ወገን ሲጎዳ ዝም ብለን አናይም በሚል መንፈስ በአፋርና አማራ ክልል ለሚገኙ ተፈናቃዮች ድጋፍ ሲያደርጉ እንደቆዩ አስታውሰዋል።

አሁን ደግሞ  4 ሚሊየን ብር ግምት ያላቸው የምግብ ቁሳቁስና 3 ሚሊዮን ብር ጥሬ ገንዘብ በክልሉ ለተፈናቀሉ ወገኖች ድጋፍ እንዲውል ማመቻቸታቸውን  ተናግረዋል።

በሽብር ቡድኑ የወደሙ የኤሌክትሪክ መሰረተ ልማቶችን በፍጥነት መልሶ በመጠገን አብዛኛው የአማራ ክልል የኤሌክትሪክ አገልግሎቱን መልሰው እንዲያገኙ ተደርጓል ብለዋል።

እንደ ዋና ስራ አስፈፃሚው ገለፃ፤ አገልግሎቱ የተቋረጠባቸው ሌሎች አካባቢዎችን አገልግሎቱን ለማስቀጠል እየተሰራ  ነው።


የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም