ቢሮው በመዲናዋ የሚገኙ ነጋዴዎች በቀራቸው አንድ ሳምንት ጊዜ ውስጥ የንግድ ፈቃዳቸውን እንዲያሳድሱ አሳሰበ

285

አዲስ አበባ፤ ታህሳስ 22 ቀን 2014 (ኢዜአ) የመዲናዋ ነጋዴዎች በቀራቸው አንድ ሳምንት የንግድ ፈቃዳቸውን እንዲያሳድሱ የአዲስ አበባ ንግድ ቢሮ አሳሰበ፡፡

ቢሮው እስከ ታህሳስ 30 ቀን 2014 ዓ.ም የንግድ ፍቃዳቸውን በማያሳድሱ ነጋዴዎች ላይ ህጋዊ እርምጃ እንደሚወስድም አሳውቋል፡፡

በቢሮው የንግድ ምዝገባና ፍቃድ ዳይሬክተር አቶ ብርሃኑ ተገኝ ለኢዜአ እንደገለጹት፤ በየዓመቱ ከሐምሌ 1 ቀን እስከ ታህሳስ 30 ቀን ያለው ጊዜ ፍቃድ የሚታደስበት ወቅት ነው፡፡

በዚህም እስከ ታህሳስ 30 ቀን 2014 ዓ.ም የንግድ ፍቃድ ማሳደስ የሚጠበቅባቸው ከ400 ሺህ በላይ ነጋዴዎች ቢኖሩም እስከ አሁን ድረስ ፍቃዳቸውን ያሳደሱት 270 ሺህ ብቻ መሆናቸውን ገልጸዋል፡፡

የዕድሳት ጊዜውን የማያከብሩ ነጋዴዎች ከጥር 1 ቀን ጀምሮ 2 ሺህ 500 መቶ ብር ቅጣት እንደሚጣልባቸው አውቀው በቀራቸው አንድ ሳምንት ውስጥ ፍቃዳቸውን እንዲያሳድሱ አሳስበዋል፡፡

ፍቃድ የሚታደስበት ቀነ ገደብ እየተጠናቀቀ መሆኑን ተከትሎ በርካታ ነጋዴች እየመጡ መሆኑን ኃላፊው ጠቁመዋል፡፡

በዚህም ደንበኞች ወረፋ በመጠበቅ እንዳይጉላሉ እስከ ወረዳ ያሉ ባለሙያዎች በንቃት እየሰሩ ይገኛሉ ብለዋል፡፡

ባለሙያዎቹ የእረፍት ቀንን ጨምሮ ከመደበኛ የስራ ሰዓት ውጭ አገልግሎት እየሰጡ እንደሚገኙም አስረድተዋል፡፡

ፍቃድ የሚያሳድሱ ደንበኞች በአካል መምጣት ሳይጠበቅባቸው ግብር የከፈሉበትን ክሊራንስ በመያዝ በበይነ መረብ በwww.etrade.gov.et በመጠቀም አገልግሎት ማግኘት እንደሚችሉ አሳውቀዋል፡፡  

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም