ዳያስፖራዎች በደቡብ ኦሞ ዞን የሚገኙ ገፀ በረከቶችንና ማራኪ የቱሪስት መዳረሻዎችን እንዲጎበኙ ጥሪ ቀረበ - ኢዜአ አማርኛ
ዳያስፖራዎች በደቡብ ኦሞ ዞን የሚገኙ ገፀ በረከቶችንና ማራኪ የቱሪስት መዳረሻዎችን እንዲጎበኙ ጥሪ ቀረበ

ጂንካ ፤ታህሳስ 22/2014 (ኢዜአ) የጠቅላይ ሚኒስትሩን ጥሪ ተቀብለው ወደ ሀገር ቤት የሚመጡ ዳያስፖራዎች በደቡብ ኦሞ ዞን የሚገኙ ገፀ በረከቶችንና ማራኪ የቱሪስት መዳረሻዎችን እንዲጎበኙ ጥሪ ቀረበ።
የደቡብ ኦሞ ዞን ባህል፣ቱሪዝምና ስፖርት መምሪያ ኃላፊ አቶ ዳንኤል ዶብዮ ለኢዜአ እንደገለጹት፤ የዳያስፖራዎችን የቆይታ ጊዜ ያማረ የሚያደርጉ የመስህብ መዳረሻዎች በዞኑ ይገኛሉ።
ዞኑ በቱባ ባህሎች፣ በታሪካዊ ቅርሶች እና በተፈጥሮ ፀጋዎች የታደለ መሆኑን ጠቁመው፣ በተለይ የማጎ ብሔራዊ ፖርክ መገኛ በመሆኑ ብርቅዬ አዕዋፋትና የዱር እንስሳት መኖራቸውን ጠቅሰዋል።
ለእይታ የሚማርኩ መልከዓ ምድራዊ ገፅታዎች፣ ፏፏቴዎች፣ የተፈጥሮ ዋሻዎች እና ለጤና ተስማሚ የሆኑ ፍል ውሃዎችም የዞኑ ሌላው መስህቦች መሆናቸውን አመላክተዋል።
ኃላፊው እንዳሉት፤ የ "ክብሽ ፈጀጅ የአንትሮፖሎጂ ሳይቶች"ም በዞኑ ታሪካዊ የሰው ዘር መገኛ ደሴቶችና የቱሪስት መዳረሻዎች ናቸው።
ዳያስፖራዎች ወደ ዞኑ ሲመጡ እነዚህን ከመጎብኘት ባለፈ በሐመር ብሔረሰብ ኢቫንጋዲ ባህላዊ የምሽት ጭፈራ ራሳቸውን በማዝናናት ሀሴት መጎናጸፍ እንደሚችሉ ነው ያስታወቁት።

የሙርሲ ብሔረሰብ የዱላ ምክክቶሽ ውድድር እንዲሁም የቦዲ ብሔረሰብ '' ኬኤል'' የተሰኘው የባለፀግነት የውፍረት ውድድር ቀልብ የሚስቡ ትዕይንት መሆናቸውንም ኃላፊው ገልጸዋል።
በተጨማሪም በዞኑ የሚገኙ 16 ብሔረሰቦችን የአመጋገብ፣ የአለባበስ፣ የአጋጌጥ፣ የቤት አሰራር፣ ባህላዊ የግጭት አፈታት ዘዴዎች እና ባህላዊ ክዋኔዎች ሌሎቹ የቱሪስት መስህቦች መሆናቸውን ነው ያመለከቱት።
ማራኪ የተፈጥሮ ፀጋ ባለቤት ወደሆነው ዞን መጥተው ቢጎበኙ መንፈሳቸውን ከማደስ ባለፈ የሀገሩን ባህል፣ ታሪክና ቅርስ የሚያውቁበት መሆኑን የገለጹት አቶ ዳንኤል ፤ ዳያስፖራው ማህበረሰብ ወደ አካባቢው በመምጣት እንዲጎበኙ ጥሪ አቅርበዋል።
የዞኑ ህዝብ ለጉብኝት የሚመጣውን ዳያስፖራ በኢትዮጵያዊ የእንግዳ አቀባበል ባህል መሰረት ተቀብሎ ለማስተናገድ ዝግጅት ማድረጉን አስታውቀዋል።
"በተመጣጣኝ ዋጋ አገልግሎት የሚሰጡ ዘመናዊ ሆቴሎችና ሪዞርቶች መዘጋጀታቸውን ጠቁመው፣ ፀጥታን በማስከበር በኩልም የጸጥታ አካላት የዝግጅት ሥራ ማጠናቀቃቸውን አስታውቀዋል።
በጂንካ ከተማ የናሳ ሆቴል ሥራ አስኪያጅ ወይዘሮ ትዕግስት ፍርዱ ለኢዜአ በሰጡት አስተያየት ፤ዳያስፖራዎች ቆይታቸው ያማረና የተሳካ እንዲሆን አስፈላጊውን ዝግጅት ማድረጋቸውን ተናግረዋል።
የእሳቸውን ሆቴል ጨምሮ በዞኑ የሚገኙ ሆቴሎች እና ሪዞርቶች ከሚሰጡት የአገልግሎት ክፍያ ላይ የ30 በመቶ ቅናሽ በማድረግ እንግዶችን ለመቀበል የጋራ መግባባት ላይ በመድረስ እየተጠባበቁ መሆኑንም ገልጸዋል።
በውጭ የሚኖሩ ኢትዮጵያዊያንና ትውልደ ኢትዮጵያዊያን ወደ ሀገር ቤት እንዲመጡ ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ አህመድ ባደረጉላቸው ጥሪ መሰረት ብዙዎች መግባታቸውንና በመግባት ላይም እንደሚገኙ ታውቋል።