ኅብረተሰቡ ለበዓል የሚፈልጋቸው ምርቶች በሸማቾች ኅብረት ስራ ማኅበራት ይቀርባሉ

63

አዲስ አበባ ታህሳስ 21/2014(ኢዜአ) ለገና በዓል የሚያስፈልጉ የተለያዩ ምርቶች በሸማቾች ኅብረት ስራ ማኅበራት በኩል እንደሚቀርቡ የኢትዮጵያ ኅብረት ስራ ኮሚሽን ገለፀ።

የኮሚሽኑ ምክትል ዋና ዳይሬክተር አብዲ ሙመድ ለኢዜአ እንደገለጹት በገና በዓል ኅረተሰቡ የሚፈልጋቸውን ምርቶች በበቂ ሁኔታ ለማቅረብና የገበያውን ዋጋ ለማረጋጋት በኅብረት ስራ ማኅበራት ዝግጅት ተደርጓል።

በዓላትን አስታኮ የሚኖረውን የዋጋ ጭማሪና የአቅርቦት እጥረት ለመፍታትም የሸማቾች ኅብረት ስራ ማኅበራት ምርቶችን በስፋት ለማቅረብ ተዘጋጅተዋል።

በዚሁ መሰረት በአዲስ አበባ ከ6 ሚሊዮን ሊትር በላይ ዘይት፣ ሽንኩርት፣ ዶሮ በኅብረት ስራ ማኅበራቱ ይቀርባሉ ብለዋል።

በተጨማሪም እንቁላል፣ ቅቤ፣ የስንዴ ዱቄት እና የእርድ በሬዎችም በማኅበራቱ እንደሚያቀርቡ ነው የገለጹት።

ኅብረተሰቡ ለበዓል የሚያስፈልጉ ምርቶችን በእሁድ ገበያዎችና በሸማቾች ኅብረት ስራ ማኅበራት መደብሮች ማግኘት እንደሚችል ጠቁመዋል።

እንደ አቶ አብዲ ገለጻ በአማራ፣ በኦሮሚያ፣ በሲዳማና በደቡብ ክልሎች ደግሞ የተለያዩ ምርቶች ለማቅረብ ዝግጅት ተደርጓል።

ምርቶችን እስከ በዓሉ ዋዜማ ድረስ ለኅብረተሰቡ ተደራሽ ለማድረግ በሁሉም ቀናት ገበያ እንደሚኖርም ጠቁመዋል።

ኅብረተሰቡ ሰው ሰራሽ የምርት እጥረት የሚፈጥሩና በኢኮኖሚ አሻጥር የሚሳተፉ ነጋዴዎችን ለሕግ አካላት በመጠቆም ተጠያቂ እንዲያደርግም አሳስበዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም